መገናኛ ብዙሃን ለኢትዮጵያ ህልውና እና ብልፅግና ሊተጉ ይገባል – ዲያቆን ዳንኤል ክብረት

You are currently viewing መገናኛ ብዙሃን ለኢትዮጵያ ህልውና እና ብልፅግና ሊተጉ ይገባል – ዲያቆን ዳንኤል ክብረት

AMM – መጋቢት 4/2018 ዓ.ም

የጠቅላይ ሚኒስትሩ የማህበራዊ ጉዳዮች አማካሪ ሚኒስትር ሙዓዘ ጥበባት ዲያቆን ዳንኤል ክብረት መገናኛ ብዙሃን ለኢትዮጵያ ህልውና እና ብልፅግና ሊተጉ እንደሚገባ አስገነዘቡ፡፡

የመገናኛ ብዙሃንና የተቋማት አመራሮች “መገናኛ ብዙሃን ለብሔራዊ ጥቅም” በሚል መሪ ሀሳብ ሀገር አቀፍ የመገናኛ ብዙሃን ኮንፈረንስ አካሂደዋል፡፡

በኮንፈረንሱ ላይ ንግግር ያደረጉት አማካሪው ፣ የተሻለች ኢትዮጵያን ለመገንባት በሚደረገው ጉዞ ሚዲያዎች በዋናነት የኢትዮጵያን ብሄራዊ ጥቅም ለማስከበር፤ ህብረ ብሄራዊ አንድነትን ለማፅናት፣ የወል ትርክትን ለማጎልበት እና ኢትዮጵያን ለማበልፀግ በሚደረጉ እሳቤዎች ላይ የበለጠ ትኩረት ሰጥተው ሊሰሩ እንደሚገባ አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡

የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ወይዘሮ ሀይማኖት ዘለቀ በበኩላቸው፣ መንግስት ለዘርፉ እያደረገ ያለውን ድጋፍ አንስተው፤ በቀጣይም ሚዲያዎች ቀጣናዊ ሁኔታዎችን በአግባቡ በመረዳት የታሪክ ጠላቶች የሚነዙትን አደገኛ መረጃ የመቀልበስና ለብሄራዊ ጥቅም ዘብ የመቆም ኃላፊነት እንዳለባቸው አሳስበዋል።

በዘርፉ ያሉ ፈተናዎችን በጋራ በመወያየት ወደ ድል መቀየር፣ በብልሃትና በንቃት የጠላቶችን አፍራሽ አጀንዳ የሚመክቱ እንዲሁም በእውቀትና በሀገር ፍቅር ስሜት ለብሄራዊ ጥቅም የሚሟገቱ ባለሙያዎችንና ተቋማትን በጥራት ማብዛት እንደሚገባም ዋና ዳይሬክተሯ ተናግረዋል፡፡

ከኤ ኤም ኤን ጋር ቆይታ ያደረጉት የውይይቱ ተሳታፊዎች በበኩላቸው፣ ሀገር ከማንኛውም አመለካከት በላይ መሆኗን አንስተው፣ የብሄራዊ ጥቅምን እሳቤ ለማስረጽ በትጋት እንደሚሰሩ ቃል ገብተዋል።

በአስማረ መኮንን

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review