ከወንዞቿ የታረቀች ከተማ

You are currently viewing ከወንዞቿ የታረቀች ከተማ

“የወንጀለኞች መሸሸጊያና የቆሻሻ መጣያ የነበረውን ስፍራ፤ ውብ፣ ለዐይን ማራኪ እና የቱሪስት መስህብ አድርገን ገንብተነዋል”
የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ ወይዘሮ አዳነች አቤቤ

ወንዞች ለብዙ ከተሞች የመኖራቸው ማረጋገጫ የልብ ምት፣ የዜማቸው ማጣፈጫ ቅኝት፣ የፍቅራቸውን ሙዳይ መስሪያ አለላና አክርማ፣ የዕድገታቸውን ጎጆ መቀለሻ ካስማ፣ የብልፅግናቸው መታወቂያ ዓርማ፣ ደህንነታቸውን መጠበቂያ ማማ እና ስልጣኔያቸውንም ማሳያ መስታወት ናቸው፡፡

ለዚህ ደግሞ የምድራችንን ውብ ከተሞች የታሪክ መዝገብ ስንገልጥ እና የዛሬ ዝናቸውን ስናደምጥ ይህንን እውነት እናገኛለን፡፡ “የሀገር ፀጋ የሀገር ልብስ” እንዳለችው ድምፃዊት እጅጋየሁ ሽባባው፣ የዓባይ ወንዝ ለካርቱም፣ ካይሮና አሌክሳንደሪያ ከተሞች የውበታቸው ሰገነት፣ ምግብና መጠጣቸው ነው፡፡ ዛሬ ደግሞ ለኢትዮጵያ ልብሷም ጉርሷም መሆኑ ሳይዘነጋ፡፡

ወደ አውሮፓ ከፍ ብንልም የቴምዝ ወንዝ የለንደን ታሪክ እና ባህል ዓርማ ነው። ከ321 ኪሎ ሜትር በላይ የሚሸፍነው ይህ ወንዝ ከተማዋን እያረሰረሰ፣ ፈገግታን በፊቷ ላይ እየነሰነሰ እና ደስታዋን እየጨመረ በስስት እያያት አቋርጧት ያልፋል፡፡

በወንዙ ዳር ያሉ ፓርኮች፣ የእግረኛ መንገዶች፣ መሰል የሰውን ልጅ በሀሴት የሚያረሰርሱ መናፈሻዎች ለለንደን ከተማ ነዋሪዎች ብቻ ሳይሆኑ ለጉብኝት፣ ለስብሰባና ለልዩ ልዩ ጉዳዮች ወደ ከተማዋ ለሚመጡ እንግዶች ተመራጭ መዳረሻዎች፣ ጭንቀትና ናፍቆትን ማስረሻዎች እና ተበልቶ የማያልቅ የልቦና ማዕድ ናቸው፡፡

በአምስተርዳም የአምስቴል ወንዝ ለከተማው የውበት ምንጭ ነው፤ በወንዞቹ ዳርና ዳር ያሉ ታሪካዊ ሕንፃዎች እና ድንቅ ስፍራዎች በየዓመቱ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ጎብኚዎችን የሚስብ ልዩ ውበትን ፈጥረዋል። የአምስቴል ወንዝ ለከተማዋ የውበት ምንጭ ብቻ አይደለም፤ ከጫፍ እስከ ጫፍ መመላለሻና ካሰቡት መድረሻ መንገድም እንጂ፡፡

የሞስክቫ ወንዝ በሞስኮ እምብርት ውስጥ የተንሰራፋ እና የከተማዋን የህንፃ ጥበብ በውሃ መስታወትነት የሚያሳይ ድንቅ ፀጋዋ ነው፡፡ የወንዙ ዳርቻዎች በመናፈሻ ቦታዎች፣ በእግረኛ መንገዶች እና በባህላዊ ተቋማት የተሞሉ በመሆናቸው ከተማዋን የእንቅስቃሴ ማዕከል አድርጓታል፡፡ ይህ ወንዝ በደማቋ ከተማ ውስጥ በተፈጥሮ እና በከተማ ህይወት መካከል ያለውን ጣፋጭ መስተጋብር የሚያሳይ ዋቢ ምስክርም ሆኖ ያገለግላል፡፡

እውቋ ብራዚላዊት የስነ ሕንፃ እና የከተማ ፕላን ተመራማሪ ቲፋኒ ኒኮሊ፣ ‘The value of urban rivers: European experiences and a South American perspective’ በሚል ርዕስ ባሳተሙት ጥናታዊ ጽሑፋቸው እንደገለፁት፣ በብዙ የአውሮፓ ዋና ከተሞች ያሉ ወንዞች የውበት፣ የሀብት፣ የሰው ልጆች ብቻ ሳይሆን የዓሳም፣ የሀሳብም መመላለሻ ናቸው፡፡ ለዚህ ደግሞ በፓሪስ፣ በለንደን፣ በስቶክሆልም፣ በኦስሎ እና መሰል ከተሞች ያሉ ወንዞችን መጥቀስ ይቻላል፡፡

ወንዞች ለዓለማችን ታላላቅ ከተሞች የውበትም የሀብትም ምንጭ እንደሆኑ አያሌ አብነቶችን መጥቀስ ብንችልም፣ አዲስ አበባ ከተማና ወንዞቿ ግን ለዚህ የታደሉ አልነበሩም፡፡ ከአዲስ አበባ ወንዞች የሚፈልቀው ደስ የማይል ሽታ በውሃ ውስጥ ከፍተኛ ብክለት መኖሩን የሚያሳይ እንደሆነ ተደጋግሞ የተነገረ ሀቅ ነው፡፡ ይህ መጥፎ ሽታ የከተማዋን ገጽታ ከማበላሸት አልፎ የህብረተሰብ ጤና ጠንቅ ስለመሆኑም ምስክር አያሻውም፡፡

መዲናዋ ግን የወንዝ ሀብታም ናት፡፡ መረጃዎች እንደሚያሳዩት በአዲስ አበባ 7 ትልልቅና ከ76 በላይ ትንንሽ ወንዞች ቢኖሩም ለከተማዋ ውበትና ሀብት መሆን ግን አልቻሉም ነበር፡፡ ከታላላቅ ወንዞቿ መካከልም ቀበና፣ ባንተይቀጡ፣ ቀጨኔ፣ ቁርጡሚ፣ ቡልቡላ፣ አቃቂ እና የቄራ ወንዞችን መጥቀስ በቂ ነው፡፡

በመዲናዋ የተጀመረው የወንዝ ዳርቻ ልማት ግን የአዲስ አበባ ወንዞችን ወደ ሞት ሳይሆን ወደ ውበት፣ ወደ ብክለት ሳይሆን ወደ ሀብት እንዲፈስሱ የሚያደርግ ዕድል እንደሆነም ብዙዎች በመመስከር ላይ ናቸው፡፡

ለአብነትም ባሳለፍነው ማክሰኞ አመሻሽ ላይ በቴዎድሮስ አደባባይ አካባቢ እጅግ ዘመናዊ ሆኖ የተገነባው የድል ፕላዛ እና የቁርጡሚ የወንዝ ዳርቻ ልማት ተመርቋል፡፡ በዚሁ ወቅት የአዲስ አበባ ከንቲባ ወይዘሮ አዳነች አቤቤ ባስተላለፉት መልዕክት “በአንድ ወቅት የወንጀለኞች መሸሸጊያና የቆሻሻ መጣያ የነበረውን ስፍራ ዛሬ ውብ፣ ለዐይን ማራኪ እና የከተማችን አንዱ የቱሪስት መስህብ አድርገን ገንብተነዋል።” ብለዋል፡፡

የአፍሪካ ልማት ባንክ “Addis Ababa Beautifying Sheger River Development Project” በሚል ርዕስ ጥቅምት 17 ቀን 2022 እ.ኤ.አ. ይፋ ባደረገው ጥናታዊ መረጃ መሰረት ቁርጡሚ እና የቀበና ወንዞች ጥቅጥቅ ባሉ ሰፈሮች ልብ ውስጥ የሚፈስሱ ናቸው፡፡ በዚያው ልክ ከመኖሪያ ቤቶች እና ከተለያዩ ኢንዱስትሪዎች የሚወጡ ቆሻሻዎች የወንዞቹን ተፈጥሯዊ መልክና መዓዛ ቀይረውት ለብዙዎች የጤና እክል ምክንያት ከመሆናቸውም ባሻገር፣ በዙሪያቸው የሚኖሩ ሰዎች በዝናብ ወቅቶች ለከፍተኛ የጎርፍ አደጋ ይጋለጡ እንደነበርም በመረጃው ተመላክቷል፡፡

“ዓሳ አበላሻለሁ ዓባይ ዳር ነው ቤቴ…” እንዲል የሀገሬ ሰው፣ ‘ቁርጡሚ’ በአፋን ኦሮሞ ቋንቋ ዓሳ ማለት ሲሆን፣ ምንም ተጨማሪ መረጃ ሳያስፈልገን ይህ ወንዝ ዓሳዎች እንደልባቸው የሚፈነጩበት፣ በዘመኑም የአካባቢው ነዋሪዎች ምግብና መጠጣቸውን የሚያገኙበት የሜዳ ላይ ማጀት ነበር ማለት ነው፡፡

የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ባሳለፍነው ወር ይፋ ባደረገው መረጃ መሰረትም በኢትዮጵያ እየተከናወነ ያለው የወንዝ ዳርቻ ልማት የወንዝ ተፋሰሶችን ከብክለት አጽድቶ ማከም እና መልሶ ህያው ከማድረግ ባሻገር፣ በታየ ሁሉን አቀፍ ርዕይ የተመራ ነው። ይህ አሰራር በወንዝ ዳርቻዎች የመሠረተ ልማቶችን በማስተሳሰር ላይ ያተኩራል። በሁለቱ አቅጣጫ የወንዝ ዳርቻዎች እንደየሁኔታው 50 ሜትር የመተንፈሻ እና መናፈሻ ዞኖች የተሰናዱበትም ነው። በእነዚህ ኮሪደሮች ያለውን የመሬት አጠቃቀም በማደራጀት ብክለትም ሆነ የጎርፍ ስጋትን ለማስወገድ በሚያስችል ሁኔታ ተሰርቷል። የቀደመውን ሥነ ምኅዳር ለመመለስ፣ ህዝባዊ ስፍራዎችን ለመገንባት፣ የመንቀሳቀሻ መንገዶችን ለማቆራኘት ብሎም የኢኮኖሚ እድሎችን ለማስፋት ጥረት ተደርጓል። ይህ እንደየተጨባጭ ሁኔታው በመለዋወጥ እና ምሉዕነት ባለው እይታ የተፈፀመ ዘዴ የወንዝ ዳርቻዎችን ዘላቂ የከተማ ልማትን እና የማኅበረሰብ ደኅንነትን የሚደግፉ፣ በሚገባ የሚመሩ፣ ምርታማ፣ ለኑሮ የተመቹ ከባቢዎች አድርጓቸዋል።

ለዚህ ደግሞ በአዲስ አበባ ከቀበና ድልድይ እስከ እንጦጦ ተራራ ያለው የወንዞች ዳርቻ ልማት እና ባሳለፍነው ማክሰኞ የተመረቀው የቁርጡሚ የወንዝ ዳርቻ ልማት በቂ ምስክር ናቸው፡፡ 2 ነጥብ 2 ኪሎ ሜትር ርዝመት ያለው የቁርጡሚ የወንዝ ዳርቻ ልማት የተለያዩ የሕዝብ አገልግሎት መስጫዎችን፣ የሕፃናትና የአዋቂዎች ስፖርት ማዘውተሪያዎችን አካትቶ በጽዱና በቆንጆ ሁኔታ ተገንብቷል።

ፕሮጀክቱ የህፃናት መጫወቻ፣ የስፖርት ሜዳ፣ 5 አምፊ ቴአትር፣ የህፃናት ማቆያ (daycares)፣ የህዝብ መፀዳጃ ቤቶች፣ ወደ ጎላ ሚካኤል የሚሻገር ድልድይ እና 4 ኪሎ ሜትር የእግረኛ መንገድ ማካተቱን የጠቀሱት የአዲስ አበባ ከንቲባ ወይዘሮ አዳነች አቤቤ፣ ስለ ከተሜነት ስናወራ የተሳለጠ መሰረተ ልማት ያለው፣ የህዝብ የጋራ መገልገያ ስፍራዎች ያሉት፣ የስራ እድልን የሚፈጥር ንፁህ፣ ውብ፣ ምቹ መኖሪያ እና ጤናማ አካባቢን መፍጠር እንደሆነም ገልፀዋል፡፡

ከአዲስ ልሳን ጋዜጣ ዝግጅት ክፍል ጋር ቆይታ ያደረጉት የጅማ ዩኒቨርሲቲ የቱሪዝምና መስተንግዶ ማኔጅመንት ትምህርት ክፍል ኃላፊ እና መምህር ደመቀ ክብሩ እንደገለፁት፣ የኮሪደር ልማቱ በመዲናዋ የተገነቡ የቱሪዝም መስህቦችን በማገናኘትና የጎብኝዎችን እንግልት በመቀነስ ከተማዋን በጎብኝዎች ተመራጭና ዓለም አቀፍ የቱሪዝም መዳረሻ እያደረጋት ነው፡፡

በተለይም እንደ ለንደን፣ አምስተርዳም እና ፓሪስን የመሳሰሉ ከተሞች የውበታቸው ምንጭ ወንዞቻቸው ናቸው። ለዓለማችን ውብ ከተሞች ወንዞች በወርቅና በእንቁ እንደተሰራ አንገት ሀብል ደምቀው የሚታዩባቸው እና በርካታ የቱሪዝም ፍሰትን የሚጨምሩባቸው የውበትም የገቢም መሰረት ናቸው። በመሆኑም በአዲስ አበባ ወንዞች ላይ እየተሰራ ያለው ልማት የከተማዋን ሁለንተናዊ ከፍታ እየጨመረው እንደሆነም ነግረውናል፡፡

የሀገሬ ሰው ወዳጁን ሲመርቅ “እደረጃው ድረስ“ ይላል፡፡ እውነት ነው፤ ከፍ ካለው መድረስ ልብ ያሞቃል። ህይወትን ያደምቃል፡፡ የሆነ ሆኖ ዛሬ የብዙዎች ትዝታ ወደሆነው ቁርጡሚ ወንዝ በአካል ተገኝቻለሁ፡፡ ወንዙን ልክ እንደ እኔ በወጉ ለተመለከተው ትናንትን፣ ዛሬን እና ነገን እንደ መፅሐፍ ተገልጦ፣ እንደ አንበሳ ደረቱን ገልብጦ፣ እንደ ጠቢብ ስለ እውነት አምጦ፣ እንደ ለጋስ ሳይሰስት፣ እንደ ዋሾ ሳይወሰልት፣ ትናንትን በዛሬ፣ ዛሬንም በነገ መነፅር እያስመለከተ ታሪክን ከነ ድፍድፉ ያጠጣናል፡፡ “ጥንት ዓሳዎች እንደ ቀይ ባህር መርከቦች የሚርመሰመሱብኝ፣ ሰዎች ደስታቸውን የሚያጣጥሙብኝ፣ ትናንት ደግሞ ጀርባቸውን ሰጥተው ቆሻሻቸውን የሚወረውሩብኝ ነበርኩ፤ ዛሬ ደግሞ እንደ ጥንቱ አምሮብኛል” ይላል፡፡

በመለሰ ተሰጋ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review