AMN – መጋቢት 04/2018 ዓ.ም
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር “በቂ የምርት አቅርቦት በተመጣጣኝ ዋጋ ለሁሉም ሸማች፤ ለዒድ በዓላችን” በሚል መሪ ሀሳብ ለ1447ኛው ዒድ ዓልፈጥር በዓል የተዘጋጀ ባዛር ተከፍቷል።
የልደታ ክ/ከተማ በተዘጋጀው የመክፈቻ ስነ-ስርዓት ላይ የተገኙት የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ንግድ ቢሮ ኃላፊ ወ/ሮ ሀቢባ ሲራጅ ከተማ አስተዳደሩ የነዋሪውን የኑሮ ጫና ለማቃለል እና ለሙስሊሙ ማኅበረሰብ የ1447ኛው የዒድ ዓልፈጥር በዓል የአቅርቦት እጥረት እንዳይኖር እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
በዚህም መሠረት ባዛሩ በከተማዋ በሚገኙ 11 ክፍለ ከተሞች ከዛሬ መጋቢት 4 ጀምሮ እስከ መጋቢት 9/2018 ዓ.ም ድረስ እንደሚቆይ ተናግረዋል።

ባዘሩ የኢንዱስትሪ እና የግብርና ምርቶችን ያካተተ ሲሆን በምርቶቹም ላይ ከነፃው ገበያው አንፃር ከ15 እስከ 20 በመቶ ቅናሽ መደረጉን ኃላፊዋ አስታውቀዋል፡፡
የከተማ አስተዳደሩ የንግድ ቢሮ፣ የአርሶ አደር እና የከተማ ግብርና እንዲሁም ኢንዱስትሪ ልማት ቢሮን ጨምሮ አምስት ተቋማት በቅንጅት የተሳተፉበት መሆኑንም ጠቁመዋል።
የልደታ ክ/ከተማ ብልፅግና ፖርቲ ፅ/ቤት ኃላፊ አቶ ዘመኑ ደሳለኝ በበኩላቸው ባዛሩ በዓልን ጠብቆ ከሚደረጉ አላስፈላጊ ዋጋ ጭማሪ እና ምርት እጥረትን የሚያስቀር እንዲሁም አምራችና ሸማችን በቀጥታ በማስተሳሰር በተመጣጣኝ ዋጋ ምርትን ለሸማቹ የቀረበበት መሆኑን ተናግረዋል።
በታምሩ ደምሴ