AMN- መጋቢት 8/2018 ዓ.ም
በከተማው በተለያዩ ስፍራዎች የሚገኙ የቅዳሜና እሁድ ገበያዎች በተለይም መሰረታዊ ፍጆታዎችን ለሸማቾች በማቅረብ የኑሮ ውድነትን እያረጋጉ ይገኛሉ።
አዲስ ሚዲያ ኔትዎርክ በአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ በሚገኙ የቅዳሜና እሁድ የገበያ ስፍራዎች ባደረገው ቅኝት፣ ሸማቾች ጥራታቸውን የጠበቁና ዋጋቸው ተመጣጣኝ የሆኑ ምርቶች በአቅራቢያቸው እያገኙ መሆናቸውን ማረጋገጥ ችሏል።
ሲሸምቱ ያገኘናቸው ሊዲያ ሱልጣን፣ በስፍራው በየሳምንቱ እየመጡ እንደሚገዙ እና ጤፍን ጨምሮ የተለያዩ ሸቀጦች በአቅርቦትም ሆነ በዋጋ ከሌላ ቦታ የተሸለ መሆኑን ይናገራሉ፡፡
ሽንኩርቱ፣ ቲማቲሙ በኪሎ ሌላ ቦታ ካለው አንፃር አቅርቦቱ ደስ እንደሚያሰኝ የገለጹት ወ/ሮ ሊዲያ፣ በትንሽ ብር ሙሉ ዘምቢል ይዘን ነው የምንሄደው ብለዋል።
መስከረም አለማየሁ የተባሉት ሌላኛዋ ሸማች፣ በየሳምንቱ ከቅዳሜና እሁድ ገበያ እንደሚገበዩ በመናገር፣ ከሌላው የአሥራ አምስትና ሃያ ብር ልዩነት እንዳለው ገልጸዋል፡፡
ገበያው ወጪ ለመቆጠብ በጣም ጠቃሚ መሆኑን በማንሳትም፣ አሁን ላይ የሚፈለጉ ምርቶች ሁሉም ሸቀጦች እየቀረቡ በመሆኑ ጥሩ ነው ይላሉ፡፡
ምርት አቅራቢዎች በበኩላቸው፣ ምርቶችን ከአምራች ወደ ተጠቃሚ በተመጣጣኝ ዋጋ እያቀረቡ መሆኑን ተናግረዋል።
አቶ ፋንታሁን ታረቀኝ እና ዳኜ በአምላክ የምርት አቅራቢዎች ሲሆኑ፣ ድንች፣ ነጭ ሽንኩርትና ቲማቲምን ጨምሮ ሁሉም የምርት ዓይነቶች እንዳሉ እና በተመጣጣኝ ዋጋ እየሸጡ መሆኑን ገልጸዋል።

ሽንኩርት በኪሎ ሰላሳ ብር፣ ቲማቲም በኪሎ ሃያ አምስት ብር፣ ድንች ኪሎ ሰላሳ አምስት እስከ አርባ ድረስ እየተሸጠ እንደሆነና ሌሎች ሸቀጦችም ልክ እንደዚሁ ቀንሰን ለማህበረሰቡ እያቀረብን ነው ብለዋል።
በአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ ወረዳ 7 የሸማች መብት ጥበቃ አባል አቶ መልካሙ መምህሬ እና በክፍለ ከተማው የወረዳ 8 የንግድ ማስፋፊያ ቡድን መሪ አቶ ደምሰው ብዙነህ፣ የረመዳን እና የዐቢይ ፆም ፍቺ በዓላትን ምክንያት በማድረግ የምርት እጥረት እንዳይከሰት ከክልል ዩኒዮኖች ጋር በቅንጅት እየተሠራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
በዘርፉ የሚሰሩ ስራዎች ውጤታማ እንዲሆኑ ከማህበረሰቡ ጋር በቅንጅት እንደሚሰራም ተመላክቷል።
በታምራት ቢሻው