AMN መጋቢት 7/2018 ዓ.ም
በኢፌዴሪ የገንዘብ ሚኒስትር አቶ አህመድ ሽዴ የተመራ የኢትዮጵያ ልዑክ በኢትዮጵያና በጣሊያን መካከል ያለውን የሁለትዮሽ ትብብር ለማጠናከር ያለመ ከፍተኛ የሥራ ጉብኝት በሮም በማድረግ ላይ ይገኛል፡፡
የገንዘብ ሚኒስትሩ አቶ አሕመድ ሽዴ በጉብኝቱ ወቅት ከጣሊያን የውጭ ጉዳይና ዓለም አቀፍ ትብብር ምክትል ሚኒስትር ኤድሞንዶ ሲሪዬሊ ጋር ተወያይተዋል።
ሁለቱ ወገኖች በሁለቱ አገራት መካከል ያለውን የቆየ አጋርነት ይበልጥ ማጠናከር በሚቻልባቸው መንገዶች ላይ የመከሩ ሲሆን፣ በተለይም በኢኮኖሚ ትብብር፣ በልማት አጋርነት፣ በግል ዘርፍ ኢንቨስትመንት መስፋፋት እንዲሁም በቀጣናዊ መረጋጋትና ትስስር ዙሪያ ትኩረት አድርገው ተወያይተዋል።
የገንዘብ ሚኒስትሩ አቶ አህመድ ሽዴ የኢትዮጵያን የማክሮ-ኢኮኖሚ ማሻሻያ መርሃ ግብር አፈጻጸም በተመለከተ ማብራሪያ የሰጡ ሲሆን፣ የማክሮ-ኢኮኖሚ መረጋጋትን ለማረጋገጥ፣ የኢንቨስትመንት ምህዳሩን ለማሻሻል እንዲሁም ቀጣይነት ያለውና ሁሉን አቀፍ የኢኮኖሚ እድገትን ለመደገፍ እየተደረገ ያለውን ጥረት አጉልተዋል።
በተጨማሪም ጣሊያን በተለያዩ የልማት መስኮች ለኢትዮጵያ እያደረገች ላለው ቀጣይነት ያለው ድጋፍ ምስጋናቸውን አቅርበዋል።

የጣሊያን የውጭ ጉዳይና ዓለም አቀፍ ትብብር ምክትል ሚኒስትር ኤድሞንዶ ሲሪዬሊ በበኩላቸው፣ የኢትዮጵያ አመራር ጠንካራ የኢኮኖሚ እድገት ለማስመዝገብ እያከናወነ ያለውን ተግባር አድንቀዋል፡፡
ሃገሪቱ በአፍሪካ ቀንድ መረጋጋትን በማምጣት ረገድ የምትጫወተውን ሚና እና ለቀጣናዊ ሰላም ያላትን ቁልፍ ፋይዳ እውቅና ሰጥተዋል።
ሁለቱ ወገኖች በኢትዮጵያና በጣሊያን መካከል ያለውን የቆየ አጋርነት ይበልጥ ለማሳደግ ያላቸውን የጋራ ቁርጠኝነት ያረጋገጡ ሲሆን፣ በጋራ ተጠቃሚነት ላይ የተመሰረተውን ትብብር ለማስቀጠል በቅርበት ለመስራት መስማማታቸዉን የገንዘብ ሚኒስቴር ለኤኤምኤን የላከዉ መረጃ ያመላክታል፡፡