AMN መጋቢት 8/2018 ዓ.ም
በኮልፌ ቀራንዮ ክፍለ ከተማ ወረዳ 07 ኮልፌ ሁለገብ የገበያ ማዕከል በሚገኘው መደብር በከፍተኛ አፍላቶክሲን (ሻጋታ) የተጠቃውና ለጤና ጉዳት ሊያደርስ የነበረ 90 ኩንታል በሬዳ ባልትና በርበሬ ገበያ ላይ ሳይሰራጭ እንደተወገደ የአዲስ አበባ ምግብ መድሃኒት ባለስልጣን አስታወቀ፡፡
የኮልፌ ምግብ መድሃኒት ቅርንጫፍ ፅ/ቤት የምግብና ጤና ነክ ተቋማት ቁጥጥር ዳይሬክቶሬት አቶ ውበት ተረፈ እንደገለፁት በሬዳ ባልትና በሚል ስያሜ የተሰጠው አምራችና አከፋፋይ ድርጅት ላይ የተወገደው በርበሬ ምርቱ ገና ገበያ ላይ ሳይቀርብ እርምጃ እንደተወሰደበት ጠቁመዋል፡፡
አምራቹ ድርጅት በ70 ኩንታል በርበሬ ላይ 20 ኩንታል ለውዝ በመቀላቀል ያዘጋጀ ሲሆን ይህም ለከፍተኛ የሻጋታ ጥቃት እንዳጋለጠው ጠቁመዋል፡፡ ምርቶቹን እርጥበታማ ባለው መደብር ውስጥ አከማችቶ በመገኘቱ እና ምርቱም በከፍተኛ አፍላቶክሲን (ሻጋታ) አንደተጠቃ ገልጸው
ይህም ለተለያዩ የካንሰር በሽታዎች የሚያጋልጥ በመሆኑ እርምጃ እንደተወሰደበት አብራርተዋል፡፡
በድርጅቱ ላይ አስተዳደራዊ እርምጃ በመውሰድ ምርቱን በማስወገድ ግለሰቡም ለህግ አካላት ተላልፎ መሰጠቱን ገልፀዋል፡፡

የአዲስ አበባ ምግብ መድሃኒት ባለስልጣን የቁጥጥር ዘርፍ ም/ስራ አስኪያጅ አቶ እንጋ እርቀታ በበኩላቸው በአያያዝ ችግር ምክንያት፣ በርበሬን በማቅለም ምንነታቸው የማይታወቅ ባዕድ ነገር ጋር የመቀላቀል ተግባር የሚስተዋል መሆኑን ባለስልጣኑ በሚያከናውናቸው የቁጥጥር አግባቦች የተገኙ ግኝቶች መሆኑን ገልፀዋል፡፡
ይህ የምግብ ክለሳ ተግባር አላግባብ ትርፍ ለማግኘት በሚፈልጉ አንዳንድ ስግብግብ ነጋዴዎች እና የሞራልና የስብዕና ጉድለት ምክንያት የሚፈጠር እንደሆነ አመላክተዋል፡፡
ማህበረሰቡም የሚሸምቷቸውን ማንኛውንም ምርቶችን ሲገዙ ልዩ ጥንቃቄ በማድረግ መሸመትና በመጠቀም ጤናቸውን ሊጠብቁ እንደሚገባ መልዕክት ማስተላለፋቸዉን ከባለስልጣኑ ያገኘነዉ መረጃ ያመላክታል፡፡