AMN – መጋቢት 8/2018 ዓ.ም
አዲስ ሚዲያ ኔትዎርክ የውስጥ አሠራሩን የሚያዘምን እና ከወረቀት ነጻ የሆነ አገልግሎት መስጠት የሚያስችለውን ስማርት ኦፊስ የተሰኘ የድረ ገጽ መተግበሪያ ይፋ አድርጓል።
የተቋሙ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ካሳሁን ጎንፋ መተግበሪያውን ሥራ ባስጀመሩበት መርሐ ግብር ላይ እንደገለጹት ሌሎች ተቋማት በቴክኖሎጂ ያመጡትን ለውጥ ከመዘገብ በመውጣት ተቋሙ የቴክኖሎጂ ተጠቃሚ በመሆኑ ደስታ ተሰምቶናል ብለዋል።
ይህ የስማርት ኦፊስ ስርዓት በተቋሙ ውስጥ ያሉ ሁሉም ሠራተኞች ከተቋሙ ሁሉም ክፍሎች ጋር እርስ በእርስ ከወረቀት ነጻ በሆነ መልኩ መረጃዎችንና ደብዳቤዎችን እንዲለዋወጡ ያደርጋል።
ተቋሙ መተግበሪያውን በመጠቀሙ የጊዜ፣ የጉልበት፣ የገንዘብ ወጪውን ለመቀነስ፣ የተቀላጠፈ አገልገሎት ለመሥጠት እና የተማከለ የመረጃ ስርዓት ለመፍጠር ያስችለዋል።
በቀጣይም የሚዲያ ተቋሙን የፋይናንስ፣ የንብረት አስተዳደር፣ የግዥ እና የተሽከርካሪ ስምሪት ክፍሎችን አሠራር የሚያዘምኑ የድረገጽ መተግበሪያዎች በሥራ ላይ ለማዋል በሒደት ላይ እንደሚገኝ ዋና ሥራ አስፈጻሚው ተናግረዋል።

የስማርት ኦፊስ አገልግሎቱ በተቋሙ ውስጥ ከዛሬ ጀምሮ በይፋ ሥራ መጀመሩን የአዲስ ሚዲያ ኔትዎርክ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ካሳሁን ጎንፋ አስታውቀዋል።