AMN መጋቢት 12/2018
ዜጎች በድምፃቸው የሚመሯቸውን ለመወሰን የምርጫ ካርድ በመውሰድ ሀገራዊ ኃላፊነታቸውን ሊወጡ ይገባል ሲሉ የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አገኘሁ ተሻገር ገለጹ።
የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አገኘሁ ተሻገር እና የሠላም ሚኒስትሩ መሀመድ እድሪስ፤ በ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ በሚወዳደሩበት ጎንደር ከተማ በመገኘት ለመራጭነት የሚያበቃቸውን ካርድ ወስደዋል።
አፈ ጉባኤ አገኘሁ ተሻገር በዚሁ ጊዜ ባስተላለፉት መልእክት፤ ለዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ መጎልበት የምርጫ ሂደት ወሳኝ መሆኑን አንስተው፤ በዚህም ዜጎች መብታቸውን መጠቀም ይኖርባቸዋል ብለዋል።
የዘንድሮው ጠቅላላ ምርጫ ሰላማዊ፣ ፍትሃዊና ዴሞክራሲያዊ በሆነ መልኩ እንዲካሄድ መንግስት በቁርጠኝነት እየሰራ መሆኑን ገልጸው፤ ይህንን እድል በአግባቡ መጠቀም እንደሚገባ ተናግረዋል።
በመሆኑም ዜጎች በድምፃቸው መሪዎቻቸውን ለመወሰን የምርጫ ካርድ በመውሰድ ሀገራዊ ሃላፊነታቸውን ሊወጡ ይገባል ሲሉም ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ ህዝብ ዴሞክራሲያዊ መብቱን በአግባቡ በመጠቀም የነገ መሪዎቹን በድምጹ ወስኖ ለመምረጥ ዛሬ ላይ የምርጫ ካርድ መውሰድ እንደሚገባም አስገንዝበዋል።
የሰላም ጉዳይ ለሁሉም ነገር መሰረት መሆኑን ያነሱት አፈ ጉባኤው ጎንደር ሠላሟን በማረጋገጥ የልማት ስራዎቿን በማከናወን ስኬት እያስመዘገበች ትገኛለች ብለዋል።

በመሆኑም የልማት ስራዎችን ለማረጋገጥና የህዝብ ተጠቃሚነትን ለማስቀጠል ሰላምን፣ ልማትንና ዴሞክራሲን አሰናስሎ መቀጠል እንደሚገባ አስገንዝበዋል።
የሰላም ሚኒስትሩ መሀመድ እድሪስ በበኩላቸው የምርጫ ሂደት የአንድ የሀገር የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ መገለጫ በመሆኑ የህዝቡ ጠንካራ ተሳትፎ ወሳኝ መሆኑን መግለጻቸዉን ኢዜአ ዘግቧል፡፡
በመሆኑም በዘንደሮው ምርጫ ዜጎች የምርጫ ካርዳቸውን ከወዲሁ በመውሰድ የነገ መሪዎቻቸውን ነፃና ዴሞክራሲያዊ በሆነ መልኩ ሊወስኑ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።