AMN – መጋቢት 12/2018 ዓ.ም
በልደታ ክፍለ ከተማ “ሳር ቤት” ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ለበርካታ ዓመታት በአንድ ጠባብ የቀበሌ ቤት ውስጥ ከአምስት የቤተሰብ አባላቶቻቸው ጋር ይኖሩ የነበሩት ወይዘሮ ሀዋ ሸሪፍ፣ “ከሞተ በላይ፣ በሕይወት ካለው በታች” ሆነው የመከራ ሕይወት ማሳለፋቸውን በምሬት ይናገራሉ።
ይኖሩበት የነበረው አንድ ጠባብ ክፍል ቤት ውስጥ አንድ ፍራሽ ብቻ ዘርግተው፣ ገሚሱ ቤተሰብ በራስጌ ገሚሱ ደግሞ በግርጌ ተፋፍገው ለማደር ይገደዱ እንደነበር ወይዘሮ ሀዋ ከኤ ኤም ኤን ጋር በነበራቸው ቆይታ ገልጸዋል።
ከመኝታ ችግር ባለፈ፣ የዕድሜያቸውና የጤናቸው ሁኔታ ችግሩን ይበልጥ አክብዶት እንደነበር አንስተው፣ በሌሊት ወደ መፀዳጃ ቤት እንኳን ለመሄድ መነሳት የማይችሉበት ደረጃ ላይ መድረሳቸውን ያወጋሉ፡፡
እንዴትም ብለው ለሊት ሲነሱም እንኳን፣ በልጆቻቸው ላይ እንዳይወድቁ ይፈሩ እንደነበር ያስታውሳሉ። ቤቱ ለኑሮ ምቹ ባለመሆኑ እና በጠባብነቱ ምክንያት ልጆቻቸው እና የልጅ ልጆቻቸው በዓላትን አብረው ለማሳለፍ ይቸገሩ እንደነበርም ይናገራሉ።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ባከናወነው “ሰው ተኮር” የልማት ሥራ፣ ወይዘሮ ሀዋ ባለ አራት ወለል ዘመናዊ ህንፃ ላይ ሰፊና ምቹ መኖሪያ ቤት አግኝተዋል። አሁን ያለሁበትን ሁኔታ ለመግለጽ ቃላት ያጥረኛል የሚሉት ወይዘሮ ሀዋ፣ ዘንድሮ ከልጅ ልጆቻቸው እና ከቅርብ ዘመዶቻቸው ጋር በአዲሱ ቤታቸው በደስታ የኢድ በዓልን ማሳለፋቸውን ገልጸዋል።

በዐረብ ሀገር ለብዙ ዓመታት ሠርታ የተመለሰችው ልጃቸውም፣ ቀደም ሲል ለእናቷ ያመጣቻቸውን እቃዎች ለማውጣት ትቸገር እንደነበር በማንሳት፣ አሁን ላይ ግን አውጥታ እናትና አባቷን ማሳመር በመቻሏ ታላቅ ደስታ እንደተሰማት ተናግራለች።
ወይዘሮ ሀዋ እና ቤተሰባቸው ይህንን እድል ላመቻቹ የከተማ አስተዳደሩ አመራሮች፣ በተለይም ለከንቲባ አዳነች አቤቤ እና ለባለሀብቶች ልባዊ ምስጋናቸውን አቅርበዋል።
ይህ ታሪክ በከተማዋ እየተከናወኑ ያሉ የልማት ሥራዎች የዜጎችን ሕይወት እንዴት እንደሚቀይሩ የሚያሳይ ህያው ምስክር እንደሆነ የእድሉ ተጠቃሚዎች የሰጡት ምስክርነት ያረጋግጣል።
በወርቅነህ አቢዮ