ከመዲናዋ ሳንባነት እስከ ዘመናዊ የእንጆሪና የንብ ልማት፤ የእንጦጦ አዲስ ምዕራፍ

You are currently viewing ከመዲናዋ ሳንባነት እስከ ዘመናዊ የእንጆሪና የንብ ልማት፤ የእንጦጦ አዲስ ምዕራፍ

AMN- ግንቦት 28/2018 ዓ.ም

አዲስ አበባ የራሷን እንጆሪ በስፋት ማምረት ጀምራለች፤ እንጦጦም የከተማዋ ሳንባ ብቻ መሆኗ ቀርቶ የልማትና የወጣቶች የሥራ ዕድል ማዕከል እየሆነች መጥታለች።

ቀደም ሲል የታረሰ መሬት ያልነበረውና የአዲስ አበባ የተፈጥሮ ሚዛን መጠበቂያ ማዕከል የሆነው ታሪካዊው የእንጦጦ ተራራ፣ ዛሬ ላይ የከርሰ ምድር ውሃ ምንጭነቱ ተጠብቆ የከተማ ግብርና ማሳያ እየሆነ ይገኛል።

በአሁኑ ወቅት በአካባቢው የተጀመረው ዘመናዊ የእንጆሪ እና የንብ ማነብ ልማት፣ ለከተማዋ አዲስ ገጽታን እያበሰረ ነው።

ይህ ከዚህ ቀደም ያልታረሰ መሬት አሁን ላይ ለአንድ ዓመት በዘለቀው ጥረት ለገበያ የሚሆን ጥራት ያለው የእንጆሪ ምርት በስፋት መስጠት መጀመሩን የእንጦጦ የወንዝ ዳርቻ ልማት የጠቅላላ እርሻ ኃላፊ አቶ ነቢል በሻህ ይገልፃሉ፡፡

አቶ ነቢል እንደገለጹት፣ የተተከሉት ችግኞች እንደየዓይነታቸው ከ2 ወር ከ10 ቀን እስከ 5 ወራት ባለው ጊዜ ውስጥ ፍሬ ማፍራት ችለዋል።

የዕድገትና የውበት ሂደቱም ማራኪ ነው፤ የእንጆሪ ምርት መጀመሪያ አረንጓዴ ሆኖ ይነሳና ወደ ቀይ ቀለም የሚቀየረው በፀሐይ ብርሃን አማካኝነት ነው።

አርሶ አደሮቹ የአየሩን ሁኔታ እየጠበቁ በጥንቃቄ በሳምንት ከ3 እስከ 4 ቀናት ምርቱን የመሰብሰብ ሥራ ያከናውናሉ።

ይህ የወንዝ ዳርቻ ልማት ፕሮጀክት፣ ምርትን ለገበያ ከማቅረብ ባለፈ፣ ሰፊ የወጣቶች የሥራ ዕድል መፈጠሪያና ዜጎች የዕለት ጉርሳቸውንና የኢኮኖሚ ተጠቃሚነታቸውን የሚያረጋግጡበት አውድ ሆኗል።

ከ100 እስከ 150 ለሚጠጉ ወጣቶች ቋሚ የሥራ ዕድል የፈጠረው ይህ ፕሮጀክት፣ ከ70 በመቶ በላይ የሴቶችን የኢኮኖሚ አቅም በማጎልበት ረገድ ትልቅ ሚና ተጫውቷል፡፡

ከዚህ ቀደም በግብርና ሥራ ላይ ተሰማርተው የማያውቁ ወጣቶች፣ አሁን ላይ በጥንቃቄና በትምህርት የታገዘ ዘመናዊ የእንጆሪ አያያዝና አሠራርን በተግባር እየተለማመዱ ይገኛሉ።

ይህ አሠራር ለሠራተኞቹ ገቢ ከመሆን ባለፈ ትልቅ የእውቀትና የክህሎት ሽግግር እየፈጠረላቸው ነው።

የእንጦጦ የወንዝ ዳርቻ ልማት በእንጆሪ ምርት ብቻ አልተወሰነም፤ ከ210 በላይ ዘመናዊ የንብ ቀፎዎችን በመያዝ ጥራቱን የጠበቀ ማር እያመረተም ይገኛል።

በአካባቢው የተተከሉ የሱፍ፣ የኑግ፣ የድንችና የተለያዩ የአበባ ዝርያዎች ለንቦቹ መልካም ቀለብ በመሆናቸው በዓመት ሁለት ጊዜ ምርታማነቱን ማረጋገጥ እንደተቻለም ተገልጿል።

እንደ ሙዝና ብርቱካን ሁሉ እንጆሪም በእያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ቤት ተደራሽ እንዲሆን ከመሥራት ባለፈ፣ ምርታማነቱ በየጊዜው እየጨመረ የሚሄድ በመሆኑ መጀመሪያ የሀገር ውስጥ ገበያን ፍላጎት በሰፊው ለማሟላት ታቅዷል።

በዚህም የሚገኘውን ትርፍ ምርት ወደ ውጭ ሀገራት በመላክ የገበያ ተደራሽነትን በዓለም አቀፍ ደረጃ ለማስፋፋት ሰፊ ቅድመ ዝግጅት መደረጉን አቶ ነቢል በሻህ ለኤ ኤም ኤን ገልጸዋል።

በወርቅነህ አቢዮ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review