AMN- መጋቢት 14/2018 ዓ.ም
በአዲስ አበባ ከተማ እየተከናወነ ያለው የኮሪደር ልማት፣ የከተማዋን ገጽታ በከፍተኛ ደረጃ ከመቀየሩ ባለፈ ለታላላቅ የጎዳና ላይ ስፖርታዊ ውድድሮች ምቹ ሁኔታን እየፈጠረ ይገኛል።
16 ሺህ ሴቶች የተሳተፉበት “ሳቅሽ ያበረታኛል” በሚል መሪ ሀሳብ ትላንት በተካሄደው የቅድሚያ ለሴቶች የ5 ሺህ ሜትር የጎዳና ላይ ሩጫ ውድድርም የከተማዋን ውበትና የነዋሪዎቿን ማህበራዊ መስተጋብር በግልጽ ያሳየ ክስተት ሆኖ አልፏል።
የኮሪደር ልማቱና መሰል የጎዳና ላይ ውድድሮች አዲስ አበባን ወደ ተሻለ የእድገትና የስልጣኔ ደረጃ እያሸጋገሯት ይገኛሉ።
ውድድሩ በሳተላይትና በተለያዩ ማህበራዊ ሚዲያዎች በቀጥታ መተላለፉ ደግሞ የአዲስ አበባን ፈጣን እድገትና አዲስ ገጽታ ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ለማስተዋወቅ ትልቅ ዕድል ፈጥሯል።
ልማቱ አዲስ አበባን ለነዋሪዎቿም ሆነ ለጎብኚዎች ማራኪ እንድትሆን ከማስቻሉም በላይ የሀገርን መልካም ገጽታ ለመገንባት ትልቅ አቅም የሚፈጥር ነው።

በተለይም በልማቱ የተገነቡት ዘመናዊ መንገዶች፣ የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራዎችና የሳይክል መጋለቢያ መስመሮች ከተማዋ ለተለያዩ ስፖርታዊ እንቅስቃሴዎች ያላትን ዝግጁነት የሚያሳዩ ናቸው።
በበረከት ጌታቸው