ሳይንሳዊ ምልከታና ጥንቃቄ ለነገው ትውልድ ዋስትና መሆኑ ተገለጸ

You are currently viewing ሳይንሳዊ ምልከታና ጥንቃቄ ለነገው ትውልድ ዋስትና መሆኑ ተገለጸ

AMN — መጋቢት 14/2018 ዓ.ም

ዛሬ የምናደርገው ሳይንሳዊ ምልከታና የጥንቃቄ እርምጃ የነገውን ትውልድ ደህንነትና ሀገራዊ ሁኔታን የሚወስን መሆኑን የኢትዮጵያ ሚቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት ገለጸ።

ኢንስቲትዩቱ ይህንን ያስታወቀው “ዛሬን መመልከት፤ ነገን ለመጠበቅ” በሚል መሪ ቃል የዓለም የሚቲዎሮሎጂ ቀንን እያከበረ ባለበት ወቅት ነው።

በዓለም አቀፍ ደረጃ ለ65ኛ፣ በሀገራችን ደግሞ ለ45ኛ ጊዜ እየተከበረ በሚገኘው በዚህ በዓል ላይ የኢንስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር አቶ ፈጠነ ተሾመ መልዕክት አስተላልፈዋል።

ዋና ዳይሬክተሩ በንግግራቸው፤ በአሁኑ ወቅት የሚከናወኑ ሳይንሳዊ ምልከታዎችና የሚወሰዱ ጥንቃቄዎች ለቀጣዩ ትውልድ ደህንነትና ለሀገራዊ ሰላም ወሳኝ ሚና እንዳላቸው አፅንኦት ሰጥተዋል።

ኢንስቲትዩቱ ላለፉት ዓመታት ለግብርና፣ ለውሃ ሀብት አስተዳደር፣ ለጤና እና ለበረራ አገልግሎቶች ስኬታማነት የላቀ አስተዋጽኦ ሲያበረክት መቆየቱንም አቶ ፈጠነ አስታውሰዋል።

ተቋሙ በየጊዜው የትንበያ አቅሙን እያሳደገ መምጣቱን የገለጹት ዋና ዳይሬክተሩ፤ ወደፊትም የቴክኖሎጂ አቅምን በመፈተሽና መረጃዎችን በአግባቡ በመጠቀም ማህበረሰቡን ከተፈጥሮ አደጋ ለመጠበቅ በትኩረት እንደሚሰራ አረጋግጠዋል።

በመጨረሻም የሚቲዎሮሎጂ መረጃ ለሀገር ሁለንተናዊ እድገት ያለው ፋይዳ ከፍተኛ በመሆኑ፤ የተጣለበትን ኃላፊነት በብቃት ለመወጣት ተቋማዊ አቅምን የማጠናከር ስራ ቅድሚያ የሚሰጠው ተግባር መሆኑን ገልጸዋል።

በፀጋ ታደለ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review