የቱሪዝም እመርታ በኢትዮጵያ

You are currently viewing የቱሪዝም እመርታ በኢትዮጵያ

AMN- መጋቢት 15 /2018

የኢትዮጵያ ቱሪዝም ትልቅ ለውጥ ውስጥ እያለፈ የሚገኝ ሴክተር ነው። መንግስት ለዘርፉ በተሰጠው ትኩረት በገቢና የስራ ዕድል ፈጠራ የኢኮኖሚው አንቀሳቃሽ ሃይል እየሆነ ይገኛል። ቱሪዝም ከሀገር ውስጥ ምርት (ጂዲፒ) 6 በመቶ ያህሉን እንደሚሸፍን ነው መረጃዎች የሚያመላክቱት።

ቱሪዝም ሚኒስቴር በ2018 ስድስት ወራት 700ሺህ የውጭ ጎብኝዎች ወደ ኢትዮጵያ መምጣታቸውንና 2 ነጥብ 6 ቢሊየን ዶላር ከዘርፉ ገቢ መገኘቱን መግለጹ የሚታወስ ነው።

አዳዲስ መዳረሻዎች መገንባት እና ነባሮቹን የማዘመን ስራዎች ፥ የመሰረተ ልማት ዝርጋታዎች ፥ በገበታ ለሸገር ፥ ገበታ ለሀገርና ገበታ ለትውልድ እና በተለይም በኮሪደር ልማቱ የተሰሩ ስራዎች ለጎብኚዎች እድገት የላቀ አስተዋጽኦ ማበርከታቸዉን መረጃዎች ያመላክታሉ፡፡

ወደ ኢትዮጵያ ከሚደረገው የጎብኝዎች ፍሰት የአዲስ አበባ ድርሻ ከፍ ያለ ነው። የዲፕሎማቶችና የትልልቅ ስብሰባዎች ማዕከል ሆና የቆየችው አዲስ አበባ ፣ ዛሬ ከፍተኛ የቱሪስት ፍሰት የሚታይባት ብቻ ሳይትሆን ጎብኚዎች ሰንብተው የሚዝናኑባት የቱሪዝም እንቁ መዲና እየሆነች ትገኛለች።

ታሪካዊነትን ከዘመናዊነት አጣጥማ የያዘችው አዲስ አበባ ፥ አዳዲስ ገጽታዎችና መዳረሻዎች ተገንበውላት የሀገሩን ሰው ብቻ ሳይሆን የዓለምን ቀልብ ለመሳብ በቅታለች።

በታላቁ ቤተ-መንግስት ግቢ ውስጥ የሚገኘው የታሪክ ሙዚየም፣ የእንስሳት መካነ-አራዊት እና የኢትዮጵያን ብዝሃነት በአንድ ስር የያዘው የአንድነት ፓርክ ፥ በዘመናዊ ዲዛይን የተገነባው ፣ ለሰላማዊ የእግር ጉዞ፣ ለሙዚቃ ኮንሰርቶችና ለቤተሰብ ቆይታ ምቹ የሆነው የወዳጅነት ፓርክ ፥ የኢትዮጵያን የወደፊት የቴክኖሎጂ ጉዞ የሚያመላክትና ለፈጠራ አሳቢዎች አይን ገላጭ የሆነው የሳይንስ ሙዚየም በከተማዋ ከተገነቡ ሜጋ ፕሮጀክቶች የሚጠቀሱ ናቸው።

በዝግባ ዛፎች የተከበበው የእንጦጦ ፓርክ ለስፖርታዊ እንቅስቃሴ፣ ለብስክሌት ግልቢያ እና ለካምፒንግ ተመራጭ ነው። ፓርኩ በውስጡ የያዛቸው ዘመናዊ ምግብ ቤቶችና የእረፍት ቦታዎች ከተማዋን ከከፍታ ላይ ሆኖ ለመመልከት ልዩ ዕድል የሚሰጡ ናቸው።

በከተማዋ ከ170 በላይ ባለ 3 ኮከብ እና ከዛ በላይ ሆቴሎች መኖራቸው ለዓለም አቀፍ ጎብኚዎች ምቹ መዳረሻ ያደርጋታል።

የአዲስ አበባ ከንቲባ አዳነች አቤቤ ለከተማዋ ምክር ቤት የስራ አፈፃፀም ሪፖርት ባቀረቡበት ወቅት ፥ በስድስት ወራት ውስጥ 700 ሺ የሚጠጉ የውጭ እና 4 ነጥብ 9 ሚሊየን የሀገር ውስጥ ዜጎች ከተማዋን መጎብኘታቸውን ተናግረዋል። 155 ቢሊየን ብር ወደ ኢኮኖሚዉ ፈሰስ ሆኗል፡፡

በተመድ የዓለም ቱሪዝም ድርጅት ባወጣው የቅርብ ጊዜ የቱሪዝም ባሮሜትር የኢትዮጵያ የቱሪዝም ዘርፍ በ15 በመቶ እድገት እንደሚያስመዘግብ ግምቱን አስቀምጧል። ይህም በአፍሪካ ተመራጭ ከሆኑ መዳረሻዎች አንዷ ያደርጋታል።

በታደሰ ሽፈራው

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review