አዲስ አበባን የሁለንተናዊ ታሪክ ማማ የማድረግ ግዙፍ ራዕይ በተግባር እየተገለጠ ነው – ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)

You are currently viewing አዲስ አበባን የሁለንተናዊ ታሪክ ማማ የማድረግ ግዙፍ ራዕይ በተግባር እየተገለጠ ነው – ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)

AMN-መጋቢት 15/2018 ዓ.ም

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በአዲስ አበባ እየተከናወኑ ያሉ ግዙፍ የልማት ስራዎች ከከተማ ውበት ባለፈ የዜጎችን አካላዊ፣ አእምሯዊና ስነ-ልቦናዊ ጤና ለመገንባት ታቅደው የሚተገበሩ መሆናቸውን ከቃና ቴሌቪዥን ጋር በነበራቸው ቆይታ አብራርተዋል።

ጤናማ የአኗኗር ዘይቤን ማዕከል ያደረገው ይህ የልማት እንቅስቃሴ፣ ከተማዋ ለነዋሪዎቿ ምቹ የሆኑ የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራዎች እንዲኖሯት በማድረግ ጤናማ የሆነ ማህበረሰብ ለመፍጠር ያለመ መሆኑን ገልጸዋል።

ጤና ማለት የአካል ብቃት ብቻ ሳይሆን የአመጋገብና የዕለት ተዕለት የአኗኗር ዘይቤ ድምር ውጤት በመሆኑ፣የመሰረተ ልማት ግንባታዎችም ይህንን እሴት ታሳቢ ያደረጉ መሆናቸውን አብራርተዋል።

የአእምሮ ጤናንና የንባብ ባህልን ለማጎልበት የተገነቡት የአብርሆት ቤተ-መጻሕፍትና የሳይንስ ሙዚየም ለነገዋ ኢትዮጵያ ያላቸው ፋይዳ ከፍተኛ መሆኑንም ጠቅላይ ሚኒስትሩ አጽንኦት ሰጥተውታል።

በአሁኑ ወቅት ወጣቶች በምሽት ቤተ-መጻሕፍት ገብተው ሲያነቡ ማየት ትልቅ ብሄራዊ ተስፋ መሆኑን የጠቀሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣የሳይንስ ሙዚየም በዓለም አቀፍ ደረጃ ትልቅ ግምት የሚሰጠውና በሳይንስ የበለፀጉ ሀገራት መሪዎች ሳይቀሩ አድናቆታቸውን የገለጹበት ስራ መሆኑን አንስተዋል።

እነዚህ ተቋማት ልጆችና ወጣቶች ከአካል ብቃት ባለፈ አዕምሯቸውን እንዲያሳድጉና በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ እንዲሆኑ ምቹ መድረክ እንደሚፈጥሩላቸውም ጠቁመዋል።

በሌላ በኩል፣ ኢትዮጵያ ያላትን ታላቅ ታሪክ የሚመጥንና ብሄራዊ ኩራትን የሚያጎለብቱ እንደ አድዋ ድል መታሰቢያና የቤተ-መንግስት ሙዚየሞች ያላቸውን ስልታዊ ጠቀሜታ አብራርተዋል።

ከዚህ ቀደም ለውጭ ሀገር የክብር እንግዶች አበባ የሚቀመጥበትና የሀገርን ታሪክ የሚናገር ስፍራ አለመኖሩ ለኢትዮጵያ አሳፋሪ እንደነበር ያስታወሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ አሁን የተገነቡት ሙዚየሞች ገንቢ ሀገራዊ ትርክት በማስረፅ ዜጎች በማንነታቸው እንዲኮሩና የአርበኝነት ስሜታቸው እንዲጎለብት ያደርጋሉም ብለዋል።

በተለይም በእንጦጦ አካባቢ እየተከናወኑ ያሉ የፈጠራ ስራዎችና የተፈጥሮ ጥበቃ እንቅስቃሴዎች የከተማዋን ገጽታ ሙሉ በሙሉ እየቀየሩት እንደሚገኙ አውስተዋል።

15 ሄክታር በሚሆን መሬት ላይ የነበሩ የባህር ዛፎችን በማጽዳትና በሀገር በቀል ዛፎች በመተካት ረገድ የተከናወነው ተግባር ለትውልድ የሚሻገር ትልቅ ቅርስ መሆኑን ገልጸው፣ በዚህ ስራ ላይ በከፍተኛ ቁርጠኝነት እየተሳተፉ ያሉ የኢትዮጵያውያን ሴቶችን ሚና አድንቀዋል።

በእንጦጦ ፓርክ ውስጥ የሚገኙት የዞማ ፓርክ፣ የባህላዊ ቅርሶች ማሳያ ስፍራዎችና የሰርከስ ማሰልጠኛ ማዕከላት ሲሰናሰሉ ከተማዋን ከፍተኛ የቱሪስትና የኢንቨስትመንት መዳረሻ እንደሚያደርጓትም አስረድተዋል።

የኮሪደር ልማትና መሰል ሜጋ ፕሮጀክቶች ዋና ግባቸው ማህበረሰቡን ሁለንተናዊ ጤናማነትን እንዲጎናጸፍ በማድረግ፣ ሰዎች በእግር እየተጓዙ ቅርሶቻቸውን እንዲመለከቱ፣ ታሪካቸውን እንዲያውቁ በማድረግ የአካል፣ የአእምሮና የሥነ-ልቦና ጤንነታቸው እንዲጠበቅ ያደርጋልም ብለዋል።

ከጤናማ ማህበረሰብ ባሻገር ታሪክን በአግባቡ ካላወቁ ስለ ሀገር የሚኖር ፍቅርና ክብር ሊጎድል ስለሚችል፣ እነዚህ ሥራዎች ዜጎች በተሟላ መንገድ ጤናማ ሆነው እንዲያድጉ በእጅጉ የሚያግዙ መሆናቸውን ጠቅላይ ሚኒስትሩ አብራርተዋል።

በሚካኤል ህሩይ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review