AMN-መጋቢት 16/2018 ዓ.ም
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ከቃና ቴሌቪዥን ጋር ባደረጉት ቆይታ፤ በአዲስ አበባ እየተከናወኑ ያሉት የኮሪደር ልማት ፕሮጀክቶች ለከተማዋ ውበትን እና ድምቀትን ከማላበስ ባለፈ፣ የኢትዮጵያን የኢኮኖሚና የማኅበራዊ መሠረት የቀየረ የብልጽግና ተምሳሌት ማሳያዎች መሆናቸውን ገለጹ።
በአዲስ አበባ የተጀመሩት የኮሪደር እና የወንዝ ዳርቻ ልማት ስራዎች እንዲሁም በከተማዋ የተሰሩት ፓርኮች ሁሉም ዜጎች ጤናማ ኑሮን እንዲመሩ ያስቻሉ ምቹና ተስማሚ ከባቢን የፈጠሩ ናቸው ብለዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ አክለው የኮሪደር ልማት ፕሮጀክቶች ከተሞችን ስማርት በማድረግ እና ስማርት የሆኑ አገልግሎቶችን የሚሰጡ መሰረተ ልማቶችን በማሟላት ለተሽከርካሪ፣ ለእግረኛ፣ ለአካል ጉዳተኛ እና ለብስክሌት የሚመቹ ዘመናዊ የትራንስፖርት ሲስተም መሰራቱን ጠቁመዋል።
በመዲናዋ የተሰሩት የወንዝ ዳርቻ የልማት ስራዎች፣ የስማርት ፖሊስ አገልግሎት መስጫ፣ የመሶብ አንድ ማዕክል አገልግሎት፣ የመንገድ ዳር መብራቶች፣ የደህንነት ካሜራዎች፣ ስክሪኖች፣ እንዲሁም የዲጂታል መታወቂያ መተግበር ፣ የስማርት ከተማነትን እና የዲጂታል ኢትዮጵያ እውን መሆን ያሳየ መሆኑንም ገልጸዋል።
ቀደም ሲል መንግሥታት ከተሞችን በሥጋት፣ ነዋሪውን ደግሞ እንደወላዋይ አድርጎ ይመለከቱ ነበር ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ አሁን ግን ከተሞች የሀገር ዉበት መገለጫ መሆናቸውን ገልጸዋል።
በሀገሪቱ እየተከናወኑ ያሉ የኮሪደር ልማት ፕሮጀክቶች የከተሞችን ገጽታ ከመቀየር ባለፈ፣ በሺዎች ለሚቆጠሩ ወጣቶች ተግባራዊ የሥራ ክህሎት ማበልጸጊያ እና ቋሚ የገቢ ምንጭ መፍጠሪያነት ማሳያ እየሆኑ መምጣታቸውንም አስረድተዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በኢትዮጵያ የተጀመሩት የኮሪደር ልማት ፕሮጀክቶች መሠረተ ልማትን ከማዘመን ባለፈ በርካታ ግቦችን ያሳኩ መሆናቸውን አሰታውሰው፣ ፕሮጀክቶቹ በግንባታ ሂደት ላይ ለሚሳተፉ ወጣቶች ሰፊ የሥራ ዕድል ከመፍጠራቸውም በላይ፣ ከመደበኛው ትምህርት በላቀ ሁኔታ ተግባራዊ የሥራ ክህሎት እንዲያገኙ አስችሏል ብለዋል።
የልማት ሥራው የመኖሪያ ቤቶች ግንባታን በማፋጠን በሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎችን የቤት ባለቤት ከማድረጉም ባለፈ፣ ዘመናዊ የትራንስፖርት መሠረተ ልማቶችን በመገንባት የጉዞ ጊዜን በመቀነስ የነዋሪዎችን ምርታማነት በከፍተኛ ሁኔታ እያሳደገ መምጣቱን ጠቁመዋል።
በተጨማሪም የቴክኖሎጂ ሽግግርን ለማፋጠን የታለመው የ”5 ሚሊዮን ኮደሮች” መርሃ ግብር እስካሁን ከ3 ነጥብ 5 ሚሊዮን በላይ ዜጎችን ማሰልጠን መቻሉ ትልቅ ስኬት መሆኑን ገልጸው፣ በአዲስ አበባ ተጀምሮ ለቀጣዩ ትውልድ እንዲሻገር የታቀደው የሸገር ወንዞች ዳርቻ ልማትም፤ በአሁኑ ወቅት በቢሾፍቱ፣ ጅማ፣ አርባ ምንጭ እና ባሕር ዳር በመሳሰሉ ከተሞችም በስፋት እየተተገበረ ይገኛል ብለዋል።
በዚህም ከተሞች የሀገር እጆችና አእምሮዎች ናቸው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ከተሞችን በሚገባ ማልማትና የሰው ኃይልን በማልማት እንዲሁም ዘመናዊ መሠረተ ልማትን በማስፋፋት የሀገሪቱን ሁለንተናዊ እና ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪነት ለማረጋገጥ መንግሥት በቁርጠኝነት እየሰራ መሆኑን አረጋግጠዋል።
በወርቅነህ አቢዮ