AMN-መጋቢት 16/2018 ዓ.ም
አዲስ አበባ በአሁኑ ወቅት በዓለም አቀፍ ደረጃ በሚጠቀስ አስደናቂ የመሠረተ ልማት ግንባታና የከተማ ለውጥ ላይ መሆኗን በኢትዮጵያ የጣሊያን ባለሙሉ ስልጣን አምባሳደር ሴም ፋብሪዚ ገለጹ።
አምባሳደሩ ይህንን ምስክርነት የሰጡት በአዲስ አበባ በመካሄድ ላይ በሚገኘው የመጀመሪያው የኢትዮጵያ እና ጣሊያን የግንባታ፣ የመሠረተ ልማት እና የከተማ መልሶ ማልማት ፎረም ላይ ተገኝተው ባደረጉት ንግግር ነው።
በንግግራቸውም ከተማዋ እያሳየች ያለው ፈጣን ለውጥ በዓለም አቀፍ የግንባታ መለኪያዎች ሲመዘን ግንባር ቀደም ከሚባሉት ከተሞች ተርታ እንደሚያሰልፋት ጠቁመዋል።
አምባሳደር ሴም ፋብሪዚ ጣሊያን በአዲስ አበባ የከተማ ገጽታ ላይ ያላትን ታሪካዊ አሻራ በማስታወስ፣ በተለይም በ1950ዎቹ እና 60ዎቹ እንደ አዲስ አበባ ማዘጋጃ ቤት እና አፍሪካ አዳራሽ ያሉ ህንፃዎችን የቀረጸውን የጣሊያናዊውን አርክቴክት አርቱሮ መዘዲሚን ስራዎች በምሳሌነት አንስተዋል።
እነዚህ ህንፃዎች የጣሊያን የፈጠራ ጥበብ እና ለኢትዮጵያ ዘመናዊ ማንነት ያበረከቱት አስተዋጽኦ ምልክት ሆነው ጸንተው እንደሚገኙ የገለጹት አምባሳደሩ፣ ጣሊያን በአሁኑ ወቅት በአዲስ አበባ እና በአጠቃላይ በኢትዮጵያ አዲስ የልማት ምዕራፍ ለመጀመር ዝግጁ መሆኗን አረጋግጠዋል።

በዚህ ከፍተኛ የልማት ፎረም ላይ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ፣ የገንዘብ ሚኒስትሩ አቶ አህመድ ሽዴ፣ የመስኖና ቆላማ አካባቢ ሚኒስትሩ አብርሀም በላይ (ዶ/ር) እና የከተማና መሰረተ ልማት ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ የትምጌታ አስራት (ዶ/ር) ጨምሮ ከፍተኛ የንግድ ልዑካን ቡድን መገኘታቸውን የኢትዮጵያ ፕረስ ድርጅት ዘግቧል፡፡
አምባሳደሩ አክለውም ጣሊያን አዳዲስ የንግድ አጋርነቶችን ለመፍጠር እና በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለውን የወዳጅነት መንፈስ ለማደስ በቁርጠኝነት እንደምትሰራ ገልጸዋል።