AMN – መጋቢት 17/2018 ዓ.ም
የአራዳ ክፍለ ከተማ አስተዳደር የአገልግሎት አሰጣጥን ግልጽነትና ተጠያቂነት ለማረጋገጥ ያለመ “እንጠያየቅ” የፊት ለፊት መድረክ አካሄደ።
በክፍለ ከተማው የፐብሊክ ሰርቪስና የሰው ሃብት ልማት እንዲሁም የኮሙኒኬሽን ጽህፈት ቤቶች በጋራ ባዘጋጁት በዚህ መድረክ ላይ፣ አመራሮችና ባለሙያዎች ከነዋሪው ማህበረሰብ ጋር በመልካም አስተዳደርና አገልግሎት አሰጣጥ ዙሪያ ቀጥተኛ ውይይት አድርገዋል።
የአራዳ ክፍለ ከተማ ፐብሊክ ሰርቪስና የሰው ሃብት ልማት ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ አስራት ነጋሳ እንደገለጹት፤ ነዋሪዎች ሳይንገላቱ ከቤታቸው ሆነው አገልግሎት እንዲያገኙ የዲጂታል ስርዓት ተዘርግቷል። በተለይም በንግድና ገቢዎች ዘርፍ ቴክኖሎጂን መሰረት ያደረገ አሰራር ተግባራዊ መደረጉን ጠቅሰዋል።
ዜጎች አገልግሎትን በነጻነትና በፍትሃዊነት ማግኘት እንዳለባቸው የገለጹት ኃላፊው፤ አገልግሎትን በአቋራጭና ባልተገባ መንገድ ለማግኘት መሞከር አገልጋዩንም ተገልጋዩንም በህግ ተጠያቂ ያደርጋል ሲሉ አስጠንቅቀዋል።

የክፍለ ከተማው ኮሙኒኬሽን ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ እንዳለ ተሰማ እንደገለጹት፤ ባለፈው “እንጠያየቅ” መድረክ ከቀረቡ 48 ጥያቄዎች መካከል 44ቱ ምላሽ ያገኙ ሲሆን፣ ቀሪዎቹ አራት ጥያቄዎች በሂደት ላይ ይገኛሉ፡፡
እንዲህ ያሉ የፊት ለፊት ውይይቶች በህዝብና በመንግስት መካከል ጠንካራ መተማመን ለመፍጠርና ውጤታማ የህዝብ አገልጋይነትን ለማስፈን እንደ ትልቅ መሳሪያ እንደሚያገለግሉ ተገልጿል።
በመድረኩ ማጠቃለያ ላይ ነዋሪዎች ከመልካም አስተዳደርና ከብልሹ አሰራር ጋር በተያያዘ ላነሷቸው ጥያቄዎች በሚመለከታቸው አካላት ምላሽና ማብራሪያ ተሰጥቶባቸዋል።
በምትኩ ተሾመ