የአፍሪካ ህብረት እና የተባበሩት መንግስታት ድርጅትን ጨምሮ ሌሎች አለም አቀፍ ተቋማት ኢትዮጵያ የባህር በር እንድታገኝ የበኩላቸዉን ሚና ሊወጡ ይገባል

You are currently viewing የአፍሪካ ህብረት እና የተባበሩት መንግስታት ድርጅትን ጨምሮ ሌሎች አለም አቀፍ ተቋማት ኢትዮጵያ የባህር በር እንድታገኝ የበኩላቸዉን ሚና ሊወጡ ይገባል

AMN – መጋቢት 18/2018 ዓ.ም

የአፍሪካ ህብረት እና የተባበሩት መንግስታት ድርጅትን ጨምሮ ሌሎች አሕጉር እና አለም አቀፍ ተቋማት ኢትዮጵያ የባህር በር እንድታገኝ የበኩላቸዉን ሚና ሊወጡ እንደሚገባ ምሁራን ገለጹ፡፡

የኢትዮጵያ የስልጣኔ ታሪክ ከቀይ ባህርና ከባህር በር ባለቤትነት ጋር በእጅጉ የተቆራኘ ቢሆንም፣ ሀገሪቱ ባለፉት ሶስት አስርት ዓመታት “የየብስ እስረኛ” ሆና መቆየቷ ይታወቃል።

በአሁኑ ወቅት ይህንን የታሪክ ስህተት ለማረም የሚደረገው ጥረት ተስፋ ሰጪ ምዕራፍ ላይ መድረሱን ተመራማሪዎችና የታሪክ ምሁራን ለኤ ኤም ኤን ገልጸዋል።

የባህር በር የሌለው ሀገር፤ በር እንደሌለው የታሸገ ቤት ነው የሚሉት የታሪክ ምሁራኑ፤ ኢትዮጵያ ለወደብ ኪራይ በየዓመቱ የምታወጣው 2.5 ቢሊዮን ዶላር ለሀገሪቱ ትልቅ የኢኮኖሚ ጫና መሆኑን ምሁራኑ ያስረዳሉ።

የታሪክ ተመራማሪው አቶ ንጉስ መኮንን አንድ ሺህ ኪሎ ሜትር የሚደርስ የባህር በር ወይም ጠረፍ እንደነበረን ይታወቃል።

በአሁኑ ወቅት የተባበሩት መንግስታትም ሆነ የአፍሪካ ህብረት ቻርተር ውሃን የመጠቀም መብታችንን ይደግፋሉ፤ ነገር ግን ይህንን በብልሃትና በዲፕሎማሲ መምራት ያስፈልጋል ብለዋል።

ሌላው የታሪክ ተመራማሪ አቶ በላይነህ ስጦታው ደግሞ ኢትዮጵያ ለአፍሪካ ሀገራት ነጻነት ባለውለታ ነች።

ከአድዋ ድል ጀምሮ የአፓርታይድ ስርዓት እስከሚወገድ ድረስ የተጫወተችው ሚና ይታወቃል። አሁን ያቺ ባለውለታ ሀገር ወደብ አልባ ሆና እያዩዋት የአፍሪካ ህብረት ፍትሃዊ ውሳኔ እንደሚያሳልፍ እናምናለን።

የሰላምና ደህንነት ተመራማሪው ሙሉጌታ አየለ(ዶ/ር) በበኩላቸው ኢትዮጵያ ሰላም ስትሆን ነው ቀጠናው ሰላም ሊሆን የሚችለው።

እንደ ኢጋድና አፍሪካ ህብረት ያሉ ተቋማት የ130 ሚሊዮን ህዝብ ባለቤት የሆነችው ኢትዮጵያ እንዴት የባህር በር እንደምታገኝ በትኩረት ሊሰሩበት ይገባል ብለዋል፡፡

የባህር በር ጥያቄው የንግድ መስመር ፍለጋ ብቻ ሳይሆን፣ ሀገሪቱን ከታሪካዊ ማንነቷ ጋር የማስታረቅና የቀጠናዊ ትስስርን የማጠናከር ግብ ያለው በመሆኑ፣ መላው ኢትዮጵያውያን ለተግባራዊነቱ በጋራ ሊሰሩ እንደሚገባ ምሁራኑ ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል።

በፍሬሕይወት ብርሃኑ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review