AMN-መጋቢት 18/2018 ዓ.ም
በምግብ ዋስትና እና ብቃት የወጣቶች የሥራ ላይ ልምምድ ፕሮግራም 15 ሺህ 492 ተጠቃሚዎች ከተረጂነት ወደ ምርታማነት መሸጋገራቸውን ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለጹ።
በአዲስ አበባ ለችግር የተጋለጡ ነዋሪዎችን ከተረጂነት ወደ ምርታማነት በማሸጋገር ረገድ ተጨባጭ ለውጥ እያስመዘገበች ትገኛለች በማለት ከንቲባ አዳነች አቤቤ ተናግረዋል።
ይህ ተግባር በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ (ዶ/ር) ይፋ ከተደረጉት አምስቱ የ“ዜሮ ግቦች” መካከል አንዱና ዋነኛው ነው ያሉት ከንቲባዋ “ተረጂነትን እና ልመናን ዜሮ የማድረግ” ታላቅ ራዕይ በከተማችን ስኬታማ እየሆነ መምጣቱን ማሳያም ነው ብለዋል።
ባለፉት አምስት ዓመታት በሴፍቲኔት ፕሮግራም ውስጥ ተይዘው ሲረዱ የነበሩ ከ695 ሺህ በላይ ነዋሪዎችን ወደ ምርታማነት በማሸጋገር ራሳቸውን እንዲችሉና ቤተሰቦቻቸውን እንዲደግፉ ተደርጓል።
በሌላ በኩል በከተማችን የሥራ ልምምድ ከተጀመረበት 2014 ዓ.ም ጀምሮ ዛሬ የተመረቁትን 8 ሺህ 852 ወጣቶች ጨምሮ 49 ሺህ የሚሆኑ ዜጎች ከተረጂነት እና ስራ አጥነት ወጥተው በተፈጠረላቸው ትስስር የሥራ ላይ ልምምድ አጠናቀው ወደ ስራ ባለቤትነት እና አምራችነት ተሸጋግረዋል ብለዋል።

የዛሬ ተመራቂዎች፤ ከተማችን እንደ እናንተ ዓይነት ትጉኅ፣ ያገኙትን ዕድል አሟጥጠው በመጠቀም ሕይወታቸውን በዘላቂነት የሚለውጡ እና ለሌላውም አርዓያ የሚሆኑ ብርቱ ወጣቶች ያስፈልጓታል በማለት ገልጸዋል።
በቀጣይም ከራሳችሁ አልፋችሁ ለሌሎች የሥራ ዕድል የምትፈጥሩ እና በሰነቃችሁት ራዕይ፣ ባካበታችሁት ልምድ የድርጅት ባለቤቶች ጭምር እንደምትሆኑ የእስካሁኑ ትጋታችሁ ትልቅ ማሳያ ነው በማለት መልዕክታቸውን በማኅበራዊ ትስስር ገጻቸው አጋርተዋል።