አዲስ መሶብ ሌብነትንና ብልሹ አሰራርን የሚያስቀር የዲጂታል መፍትሄ ነው -ጀማሉ ጀንበር (ዶ/ር)

You are currently viewing አዲስ መሶብ ሌብነትንና ብልሹ አሰራርን የሚያስቀር የዲጂታል መፍትሄ ነው -ጀማሉ ጀንበር (ዶ/ር)

AMN- መጋቢት 18 /2018 ዓ.ም

አዲስ መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት ሌብነትንና ብልሹ አሰራርን የሚያስቀር የዲጂታል መፍትሄ መሆኑን በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የፐብሊክ ሰርቪስና ሰው ሀብት ልማት ቢሮ ኃላፊ ጀማሉ ጀንበር (ዶ/ር) ገለጹ፡፡

የቢሮ ኃላፊው ከኤ ኤም ኤን ጋር በነበራቸው ቆይታ አዲስ መሶብ የተሰኘው የአንድ ማዕከል ዲጂታል አገልግሎት አሰጣጥ ተጨባጭ ውጤት እያመጣ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በ2018 ዓ.ም መስከረም ወር መጀመሪያ ላይ በይፋ ሥራ የጀመረው ይህ ዲጂታል ማዕከል፣ እስከ አሁን ድረስ ከ120 ሺህ በላይ ለሚሆኑ ዜጎች ቀልጣፋ አገልግሎት መስጠት አንደተቻለም ዶክተር ጀማሉ ገልጸዋል፡፡

በአሁኑ ወቅት በ13 የከተማ አስተዳደሩ፣ በ3 የፌዴራል እና በ2 የፋይናንስ ተቋማት ውስጥ የሚሰጡ 107 የመንግስት አገልግሎቶች በማዕከሉ መካተታቸውንም አንስተዋል፡፡

ተገልጋዮች ከአንድ ተቋም ወደ ሌላ ተቋም የሚያደርጉት ምልልስ በመቅረቱ ጊዜያቸውን፣ ወጪያቸውንና ጉልበታቸውን መቆጠብ እንዳስቻለም የቢሮ ኃላፊው ተናግረዋል፡፡

አገልግሎቱ ሙሉ በሙሉ በቴክኖሎጂ የታገዘ በመሆኑ፣ ብልሹ አሰራርንና ሌብነትን ለመከላከል ትልቅ ሚና እየተጫወተ እንደሚገኝም ጠቅሰዋል።

የቢሮ ኃላፊው አክለው እንደገለጹት፣ በቀጣይም አገልግሎቱን ይበልጥ ተደራሽ ለማድረግ ተንቀሳቃሽ የአዲስ መሶብ አገልግሎት ለመጀመር ዝግጅት እየተደረገ ነው፡፡

ባለሙያዎችም ከብልሹ አሰራር የጸዱ እንዲሆኑና በቴክኖሎጂ የታገዘ ቀልጣፋ አገልግሎት እንዲሰጡ ስልጠናና የግንዛቤ ማስጨበጥ ሥራዎች በስፋት መሰራታቸውንም ተናግረዋል፡፡

በአስማረ መኮንን

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review