AMN- መጋቢት 18/2018 ዓ.ም
በ21ኛው ክፍለ ዘመን የአንድ ሀገር የኢኮኖሚ ጥንካሬ የሚለካው በከተሞቿ ስኬት ነው። ከተሞች የኢኖቬሽን፣ የንግድ እና የኢንዱስትሪ ማዕከላት በመሆናቸው የዜጎችን የኑሮ ደረጃ የመቀየር ከፍተኛ አቅም አላቸው።
በዚህ ረገድ የኢትዮጵያ የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚ እና የማህበራዊ ማዕከል የሆነችውን አዲስ አበባን፣ በአጭር ጊዜ ውስጥ ከድህነት ወደ በለጸገ የኢኮኖሚ ማዕከልነት ከተቀየረችው የደቡብ ኮሪያዋ መዲና ሴዑል ጋር ብዙ የሚያመሳስላቸው ጉዳዮች አሉ።
የከተማ ሽግግር እንደ ኢኮኖሚ ሞተር
የደቡብ ኮሪያዋ ሴዑል ከ1960ዎቹ ጀምሮ ያደረገችው ፈጣን ዕድገት መሰረቱን ያደረገው በተቀናጀ የከተማ ፕላን እና በኢንዱስትሪዎች ላይ ነበር።
የዓለም ባንክ ሪፖርቶች እንደሚያሳዩት፣ ሴኡል የትራንስፖርት ትስስርን በማዘመን የንግድ ወጪን መቀነስ መቻሏ ለሀገሪቱ ዕድገት ቁልፍ ሚና ተጫውቷል።

አዲስ አበባም በአሁኑ ወቅት ተመሳሳይ የሽግግር ወቅት ላይ ትገኛለች። በተለይም በቅርብ ጊዜ እየተከናወኑ ያሉ የኮሪደር ልማት ስራዎች፣ ፓርኮች እና የተለያዩ ሰው ተኮር ስራዎች ከተማዋን ለኢንቨስትመንት ምቹ እያደረጓት ነው።
የከተማ መሰረተ ልማት ግንባታ ብቻ አይደለም ፣ የዜጎችን የስራ ምርታማነት የሚያፋጥን የኢኮኖሚ ሞተር መሆኑን በተግባር እያሳየች ትገኛለች።
የቴክኖሎጂ እና የዲፕሎማሲ ማዕከልነት
ሴዑል ዛሬ የዓለም የቴክኖሎጂ መዲና ናት። ይህ የሆነው መንግስት እና የግል ዘርፉ በጋራ በመሆን ለምርምር እና ለፈጠራ ስራዎች በሰጡት ትኩረት መሆኑን የኢኮኖሚ ትብብርና ልማት ድርጅት (OECD) መረጃዎች ያመለክታሉ።
አዲስ አበባም የምስራቅ አፍሪካ የዲፕሎማሲ ማዕከል መሆኗን ተጠቅማ፣ በ”አይ ሲ ቲ” መንደር እና በጀማሪ ስራ ፈጣሪዎች(Startups) አማካኝነት የቴክኖሎጂ ሽግግርን እያፋጠነች ትገኛለች።
የከተማ ዕድገት ትርጉም የሚኖረው የዜጎችን ተጠቃሚነት እርካታ ነው። ሴኡል ጥቃቅን እና አነስተኛ ተቋማትን ከትላልቅ ኩባንያዎች ጋር በማሰናሰል ሰፊ የስራ ዕድል ፈጥራለች። አዲስ አበባም በኮንስትራክሽን፣ በቱሪዝም እና በአገልግሎት ዘርፍ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ዜጎችን የስራ ዕድል ተጠቃሚ እያደረገች ትገኛለች።
ይህም የዜጎችን ፍትሃዊ ተጠቃሚነት የማረጋገጥ እና ከተሞች የዜጎች አና የሃገር ኢኮኖሚ የጀርባ አጥንት እና ሞተር ለመሆናቸው በቂ ማሳያ ነው ።
በቶለሳ መብራቴ