“ከተረጂነት ወደ ምርታማነት በማሸጋገር ረገድ ተጨባጭ ለውጥ እየተመዘገበ ነው”
የአዲስ አበባ ከንቲባ ወይዘሮ አዳነች አቤቤ
የዕለቱ የአየር ጠባይ ቀዝቃዛና ደመናማ የሚባል አይነት ነው፡፡ የአየር ሁኔታው ሳይበግራቸው በአዲስ አበባ ስታዲየም በሺዎች የሚቆጠሩ ወጣቶች፣ ሴቶችና እናቶች ተሰባስበዋል፡፡ ለእነዚህ ሠዎች የአየር ጠባይ መለዋወጥ በእንቅስቃሴያቸው ላይ ብዙም ተፅዕኖ እንደማያመጣ ገጽታቸው ይመሰክራል፡፡ ያለፉበት የሕይወት ጉዞ ለዚህ ብቻ ሳይሆን፤ ከዚህ ለላቀ ፈተና እንዳይረቱ አድርጓቸዋል፡፡ የሥራ ሰዎች፣ ሠርቶና ጥሮ አዳሪዎች ናቸው፡፡ በሥራቸው ራሳቸውን፣ ቤተሰባቸውን፣ ከተማቸውንና አገራቸውን ለመለወጥ ራሳቸውን ያበቁም ናቸው፡፡ በእነዚህ መካከል የአዲስ አበባ ከንቲባ ወይዘሮ አዳነች አቤቤ መገኘታቸው ደግሞ፤ ለተሰብሳቢዎች የበለጠ መነቃቃትን የፈጠረ ሆኗል፡፡ ቀዝቃዛው እና ደመናማው የአየር ጠባይ በአዲስ አበባ ስታዲየም በነበረው ሁነት ተረትቷል። ተስፋ፣ ሙቀት፣ ኃይልና ብርታት ሰፍኗል።
የትላንትናዋ (የመጋቢት 18 ቀን 2018 ዓ.ም.) ማለዳ ልዩ መሆኗን ከንቲባ ወይዘሮ አዳነች በሺዎች የሚቆጠሩ ወጣቶች ከተረጂነት ወደ አምራችነት መሸጋገራቸውን በማብሰር ነበር የገለጹት። በዕለቱ እንደ አዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በብቃት የወጣቶች የሥራ ላይ ልምምድ እና በምግብ ዋስትና ፕሮግራም ታቅፈው የቆዩና ያጠናቀቁ 15 ሺህ 492 ተጠቃሚዎች ተመርቀዋል። ከእነዚህ ውስጥ 8 ሺህ 852 ወጣቶች የብቃት የሥራ ልምምድ መርሃ ግብርን ያጠናቀቁ ናቸው፡፡

የተጠቃሚዎችን ምረቃ መርሃ ግብር መነሻ በማድረግ ከንቲባ አዳነች አቤቤ በይፋዊ የፌስ ቡክ ገጻቸው ላይ ባስተላለፉት መልዕክት፤ “ከተማችን አዲስ አበባ ለችግር የተጋለጡ ነዋሪዎችን ከተረጂነት ወደ ምርታማነት በማሸጋገር ረገድ ተጨባጭ ለውጥ እያስመዘገበች ትገኛለች። ይህ ተግባር በክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ይፋ ከተደረጉት አምስቱ የʻዜሮ ግቦች’ መካከል አንዱና ዋነኛው የሆነው ʻተረጂነትን እና ልመናን ዜሮ የማድረግ’ ታላቅ ርዕይ በከተማችን ስኬታማ እየሆነ መምጣቱን ማሳያ ነው” ብለዋል፡፡
በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የአዲስ አበባ ሥራና ክህሎት ቢሮ ኃላፊ አቶ ሚሊዮን ማቲዎስ በበኩላቸው ቢሮው ድህነት ዕጣ ፈንታ አለመሆኑንና በአስተሳሰብ ለውጥ ማሸነፍ እንደሚቻል የግንዛቤና የመግባባት ሥራ በመሥራቱ ተጠቃሚዎች ለለውጥ ዝግጁ እንዲሆኑ ማድረግ መቻሉን ተናግረዋል።
አቶ ሚሊዮን አክለውም ተጠቃሚዎች ወደ ሥራ ከመሰማራታቸው በፊት አስፈላጊው የስነ-ልቦና የሕይወት ክህሎትና የንግድ ሥራ ሥልጠና እንዲያገኙ ተደርጓል። ለዚህም እንደ መነሻ የሚሆን የገቢ ማስገኛ ሥራ ማስጀመሪያ ድጋፍ የተመቻቸላቸው ሲሆን ይህም ዜጎች በገበያው ውስጥ በራስ መተማመን እንዲንቀሳቀሱ አቅም ሆኗቸዋል።
በተጨማሪም ተጠቃሚዎች የሥራ ዕድል እንዲያገኙ ከመንግሥታዊ ተቋማት ባሻገር ከመንግሥታዊ ካልሆኑ ድርጅቶችና ከግል ዘርፉ ጋር የማቀናጀት ሥራ ተሠርቷል። ይህም ተጠቃሚዎች ሰፊ የገበያ ትስስርና የቴክኒክ ድጋፍ እንዲያገኙ በማድረግ ሽግግሩን ይበልጥ እንዳፋጠነው አብራርተዋል።

የምግብ ዋስትና ፕሮግራም እና የብቃት የወጣቶች የስራ ላይ ልምምድ መርሃ ግብር ተግባራዊ መሆንና ዜጎችን መጥቀም ከጀመሩ ዓመታት ተቆጥረዋል፡፡ የብቃት የወጣቶች የሥራ ላይ ልምምድ መርሃ ግብር በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር እና በዓለም ባንክ የገንዘብ ድጋፍ ከ2014 በጀት ዓመት ጀምሮ ሲተገበር መቆየቱን በማሳያነት መጥቀስ ይቻላል፡፡ መርሃ ግብሩ በቆየባቸው ጊዜያት በትላንትናው ዕለት የተመረቁትን 8 ሺህ 852 ወጣቶች ጨምሮ 49 ሺህ የሚሆኑ ዜጎች ከተረጂነት እና ሥራ አጥነት ወጥተው በተፈጠረላቸው ትስስር የሥራ ላይ ልምምድ አጠናቀው ወደ ስራ ባለቤትነት እና አምራችነት ተሸጋግረዋል።
የብቃት የወጣቶች የሥራ ላይ ልምምድ መርሃ ግብር፣ ለመዲናዋ ወጣቶች ሁነኛ የሥራ ዕድል መፍጠሪያ ሆኖ ስለማገልገሉ ከዚህ ቀደም የተከናወኑ የመርሃ ግብሩ የሁለት ዙር ፍሬያማ ውጤቶች ምስክር ናቸው፡፡ በሥራ ላይ ልምምድ መርሃ ግብር የታቀፉ ወጣቶች፡- ከሥራ አጥነት ተላቅቀው፣ የነበረባቸውን ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ስነ ልቦናዊ ጫና አስወግደው፣ ከጥገኛነት ራስን ወደ መቻል ተሸጋግረው፣ ተስፋ መቁረጥን በሥራ ስለት ቆርጠው፣ ዛሬን በጥረት ነገን በተሻለ ርዕይ ቀርፀው … ጉዞ ወደፊት የሚል ወኔን የተላበሱ የተግባር ሠዎች ወደ መሆን መቀየራቸውን ከአንደበታቸው ሰምተናል፡፡ በሥራ ቦታቸው ተገኝተን ተመልክተናል፡፡ በአሠሪ ድርጅቶች ምስክርነትም አረጋግጠናል፡፡
ነዋሪነታቸው በጉለሌ ክፍለ ከተማ የሆኑት ወጣት ገነት ረጋሳ እና ወጣት ቤተልሔም ኪዳነማርያም፣ በሦስተኛው ዙር ብቃት የወጣቶች የሥራ ላይ ልምምድ መርሃ ግብር ታቅፈው በትላንትው ዕለት በይፋ ከተመረቁት ወጣቶች መካከል ይገኙበታል፡፡ እነዚህ ወጣቶች በክፍለ ከተማው በሚገኝ ዮኬት ማኑፋክቸሪንግ ድርጅት ውስጥ በመግባት የሥራ ላይ ልምምድ ሲያደርጉ ቆይተዋል፡፡ በልብስ ስፌት ሥራ ላይ በተሠማራው ድርጅት ውስጥም ተገቢ ዕውቀት፣ ክህሎት፣ ልምድና መልካም የሥራ ስነ ምግባር በመላበስ በድርጅቱ ቋሚ ሠራተኛ ለመሆን በቅተዋል፡፡

እነዚህ ሁለት ወጣቶች እንደ ከተማ አስተዳደር ተግባራዊ በሆነው የወጣቶች የስራ ላይ ልምምድ መርሃ ግብር በእጅጉ መጠቀማቸውን በቅርቡ ከጋዜጣችን ጋር አድርገውት በነበረው ቆይታ መስክረዋል። እንደ ወጣት ገነት ረጋሳ ገለፃ፤ በመርሃ ግብሩ ከመታቀፏ በፊት የ12ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተና ተፈትና ወደ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት መግባት የሚያስችል ውጤት ባለማምጣቷ ምክንያት ተስፋ ቆርጣ በቤት ውስጥ ለመቀመጥ ተገድዳ ነበር። ከትምህርት ውጪ ምንም ዓይነት ለሥራ የሚያበቃ ሙያም ሆነ ልምድ ስለሌላት ያለሥራ ለወራት እንድትቆይ አድርጓት ነበር፡፡ ስለ መርሃ ግብሩ ያገኘችው መረጃ ያሳለፈችውን ያለሥራ በቤት የመቀመጥ አስቸጋሪ ጊዜ እንዲያከትም ምክንያት ሆኗታል፡፡
በራሷ ምርጫ ወደ አልባሳት ኢንዱስትሪ የተቀላቀለችው ወጣት ገነት፣ በመርሃ ግብሩ አማካኝነት የተለያዩ ስልጠናዎችን ወስዳለች፡፡ በሦስት ወራት የሥራ ላይ ልምምድ ቆይታዋም ጨርቅ መቁረጥ፣ ኦቨርሉክ ማድረግ እና መስፋት የመሳሰሉ መሠረታዊ ሙያዎችን በሚገባ ተክናለች። “የሥራ ላይ ልምምድ እንዳጠናቀቅሁ ድርጅቱ በቋሚነት ቀጠረኝ፤ አሁን በወር 5 ሺህ 500 ብር ደመወዝ ይከፈለኛል” በማለትም በአጭር ጊዜ ውስጥ የሙያ እና የስራ ባለቤት እንድትሆን ስላደረጋት መርሃ ግብር በኩራት ትናገራለች። ገነት አክላም አብዛኞቹ ወጣቶች በመንግስት ተቋማት መቀጠርን ብቻ እንደሚጠብቁና ይህ ሳይሳካ ሲቀር ተስፋ እንደሚቆርጡ ጠቁማ፣ በየአካባቢው ያሉ ዕድሎችን መጠቀም እንደሚገባ ትመክራለች። በቀጣይም ከምታገኘው ገቢ በመቆጠብ የግል ሥራዋን የመጀመር ትልቅ ህልም እንዳላት ገልፃለች።
የ10ኛ ክፍል ትምህርቷን ካጠናቀቀች በኋላ ለስድስት ወራት ያለ ሥራ በቤት ውስጥ መቀመጧ ለከፍተኛ ድብርትና ጭንቀት ዳርጓት እንደነበር የምታስታውሰው ወጣት ቤተልሔም ኪዳነማርያም፤ በወጣት ገነት ሃሳብ ትስማማለች፡፡ “እነዚያ ጊዜያት በጣም ረጅምና አሰልቺ ነበሩ” የምትለው ቤተልሔም፣ በሥራ ላይ ልምምድ መርሃ ግብሩ አማካኝነት ወደምትወደው የአልባሳት ሙያ በመቀላቀሏ፣ ዕድሉ ከህልሟ ጋር ለመገናኘት እንደድልድይ እንደጠቀማት ትናገራለች። አሁን ላይ ስፌት የመስፋትና ፓተርን የማውጣት ሙያን ተክናለች፡፡ ከቤተሰብ ጥገኝነት ወጥታለች፡፡ ሙያዊ ክህሎቷን፣ ዕውቀቷንና የሥራ ሥነ ምግባሯን ከማሻሻሏ በተጨማሪ፣ ከድርጅቱ ባለቤቶች ያገኘችው ልምድ ለቀጣይ ህይወቷ ትልቅ መሠረት ሆኗታል።
የብቃት የወጣቶች የሥራ ላይ ልምምድ መርሃ ግብር፣ ሥራ አጥ ወጣቶችን ከተረጂነት ወደ አምራችነት በዘላቂነት እንዲሸጋገሩ ትልቅ አቅም ከመፍጠሩ ባሻገር፤ ለአምራች እና አገልግሎት ሰጪ ተቋማት በሙያ የበቃ የሠው ኃይል እንዲያገኙ ዕድል ማመቻቸቱን የድርጅት ባለቤቶች ይናገራሉ፡፡ ወጣት ገነት ረጋሳ እና ወጣት ቤተልሔም ኪዳነማርያምን ጨምሮ 30 ወጣቶች ተቀብሎ የሥራ ላይ ልምምድ እንዲያደርጉ ያስቻለው የዮኬት ማኑፋክቸሪንግ ድርጅት ከተጠቃሚዎቹ አንዱ ነው፡፡ ከዚህ ጋር በተያያዘ የድርጅቱ መሥራችና ሥራ አስኪያጅ ወይዘሮ ቤዛዊት ነጌሶ እንዳስረዱት፣ ከሥራና ክህሎት ቢሮ የተቀበሏቸውን ወጣቶች በተቀመጠው የጊዜ ሰሌዳ መሰረት ልምምድ እንዲያደርጉ አስፈላጊውን ድጋፍና ክትትል አድርገውላቸዋል፡፡ ወደ ድርጅቱ የገቡት ወጣቶች ሙሉ ለሙሉ ልምምዱን በሚገባ በማጠናቀቃቸው፣ ሙያዊ ክህሎትንና የሥራ ሥነ ምግባርን በመላበሳቸው ሁሉም በድርጅቱ በቋሚነት መቀጠር ችለዋል፡፡ በዚህም ከድርጅቱ ጋር በሥራም፣ በሥራ ባህልም የተግባቡ ብቁ ሙያተኞችን አግኝተዋል፡፡

በአስር ሺዎች ለሚቆጠሩ ወጣቶች ቋሚ የሥራ መፍጠሪያ የሆነው የብቃት የወጣቶች የሥራ ላይ ልምምድ መርሃ ግብር፣ ለወጣቶች ቋሚና ዘላቂ የሥራ ዕድል በመፍጠር ረገድ ከፍተኛ ሚና ስለመጫወቱ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የሥራና ክህሎት ቢሮ የሥራ ስምሪት አገልግሎት ዳይሬክተር አቶ ሰብሀዲን ሱልጣን ያረጋግጣሉ፡፡ ለዚህ መርሃ ግብር ስኬታማነት የከተማ አስተዳደሩ ከንቲባ አዳነች አበቤ እና በየደረጃው ያሉ መአራሮች እንዲሁም የዓለም ባንክ ያደረገው የበጀት ድጋፍ ሚና የላቀ ሚና እንዳለው በመጥቀስ አድንቀዋል፡፡
አያይዘው እንዳብራሩት፤ የዓለም ባንክ ፕሮጀክት የመጨረሻ ምዕራፍ በሆነው የሦስተኛው ዙር የወጣቶች የሥራ ላይ ልምምድ መርሃ ግብር የታቀፉና በትላንትናው ዕለት በይፋ የተመረቁ ወጣቶች፣ የስድስት ወራት ቆይታቸውን ያጠናቀቁ እና በአሁኑ ጊዜ ሁሉም ቋሚ የሥራ ዕድል የተፈጠረላቸው ናቸው፡፡
መንግሥት የመርሃ ግብሩን ውጤታማነት በማየት፣ በመንግስት ሙሉ ወጪ የሚከናወን 4ኛ ዙር የፓይለት ፕሮግራም በ115 ሚሊዮን ብር በጀት፣ በተመረጡ 20 ወረዳዎች፣ 3 ሺህ ወጣቶችን በመያዝ መጀመሩን የገለጹት አቶ ሰብሀዲን፤ ይህ ተግባር እንደ ከተማ በአጭር ጊዜ ውስጥ የሥራ አጥነት ቁጥርን በከፍተኛ ደረጃ ለመቀነስ የሚያስችል ቁልፍ መሣሪያ መሆኑ ታምኖበታል ብለዋል።
በመጨረሻም፤ ተጠቃሚዎችን ከተረጂነት ወደ ምርታማነት የማሸጋገር ይፋዊ የምረቃ ሥነ ሥርዓት ላይ ከንቲባ ወይዘሮ አዳነች፣ የሚከተለውን መልዕክት አስተላልፈዋል፤ “ውድ ተመራቂዎች፤ ከተማችን እንደ እናንተ ዓይነት ትጉ፣ ያገኙትን ዕድል አሟጥጠው በመጠቀም ሕይወታቸውን በዘላቂነት የሚለውጡ እና ለሌላውም አርአያ የሚሆኑ ብርቱ ወጣቶች ያስፈልጓታል። በቀጣይም ከራሳችሁ አልፋችሁ ለሌሎች የሥራ ዕድል የምትፈጥሩ እና በሰነቃችሁት ርዕይ፣ ባካበታችሁት ልምድ የድርጅት ባለቤቶች ጭምር እንደምትሆኑ የእስካሁኑ ትጋታችሁ ትልቅ ማሳያ ነው፣ በርቱ!”
በደረጀ ታደሰ