ልጆች የግል ንጽህና፣ የአካባቢና የከተማ ፅዳት ወይም ንፅህና እንዴት እንደሚጠበቅና ይኸን ማድረግ ምን ጥቅም እንደሚያስገኝ ታውቃላችሁ? እናንተስ የራሳችሁንና የአካባቢያችሁን ፅዳት ምን ያህል ትጠብቃላችሁ? ያላችሁን አስተያየት ለቤተሰቦቻችሁና ጓደኞቻችሁ እንድታካፍሉ እያልን በዚህ ረገድ ያነጋገርናቸው ልጆችን ተሞክሮ እንደሚከተለው አቅርበነዋል፤ የዝግጀት ክፍላችን የግል እና የአካባቢያቸውን ንፅህና የሚጠብቁ ልጆችን ልምድና ተሞክሮ መልካም ንባብ ይሁንላችሁ፡፡
ባምላክ ተመስገን እባላለሁ፡፡ 13 ዓመቴ ነው፡፡ የጥበብ እድገት አንደኛና መካከለኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪ ነኝ፡፡ የግል ንፅህናዬን እጄንና እግሬን በመታጠብ፣ ጥፍሬን በመቁረጥ፣ ጥርሴን በመቦረሽ፣ ፀጉሬን በመታጠብ እንዲሁም ንጹህ ልብስ በመልበስ እጠብቃለሁ፡፡ ወደ ትምህርት ቤት ስሄድ ማንኛውንም አይነት ቆሻሻ መንገድ ላይ አልጥልም፡፡ ለዚህ ተብሎ በተዘጋጀ ቅርጫት ላይ አስቀምጣለሁ፡፡
ከዚህ በፊት ጉዳት እንዳለው ሳላውቅ ሙዝ ተመግቤ ልጣጩን ግቢ ውስጥ እጥል ነበር፡፡ አንድ ቀን ታላቅ ወንድሜ “እንደዚህ ሲጣል ሰዎችን አንሸራትቶ ለአደጋ ያጋልጣል” ብሎ በነገረኝ መሰረት በአግባቡ አስወግዳለሁ፡፡ ይህን በማድረጌ ደግሞ ጤናዬ የተጠበቀ ሆኗል። በየጊዜው አያመኝም፡፡ ስለዚህ ልጆች፤ ቆሻሻን በቆሻሻ መጣያ ቅርጫት ውስጥ መጣል አለባቸሁ፡፡
ሸዋዬ ተሾመ እባላለሁ፡፡ 12 ዓመቴ ሲሆን የምማረውም በጥበብ እድገት አንደኛና መካከለኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ነው። በየትኛውም ጊዜና ቦታ በትምህርት ቤትም ይሁን በቤት ውስጥ እጄን በሳሙናና በውሃ የመታጠብ ልምድ አለኝ። ቆሻሻ በየቦታው አልጥልም፤ መጣያ ቅርጫት እስከማገኝ በእጄ እይዘዋለሁ፡፡
ራሴን ንፁህ አድርጌ አካባቢዬን ማቆሸሽ እንደሌለብኝ አምናለሁ፡፡ ራሴን ንፁህ ማድረጌና አካባቢዬን አለማቆሸሼ በንጽህና ጉድለት ከሚመጣ በሽታ እንድጠበቅ፣ ትምህርቴንም በአግባቡ እንድከታተል አድርጎኛል፡፡
ዳግም ሳምሶን እባላለሁ፡፡ ንፅህና ከራስ ይጀምራል፡፡ በዚህም የግል ንጽህናዬን ከራስ ፀጉሬ እስከ እግር ጥፍሬ ድረስ እጠብቃለሁ፡፡ የግል ንፅህናዬን እንደምጠብቀው ሁሉ የምኖርበትን አካባቢ፣ የምማርበትን ትምህርት ቤት፣ በምንቀሳቀስባቸውን ቦታዎች ሁሉ ንፁህ እንዲሆኑ ቆሻሻን በየቦታው ባለመጣል ኃላፊነቴን እወጣለሁ፡፡ ቤተሰቦቼም ስለንፅህና አጠባበቅ ሁልጊዜ ይነግሩኛል፡፡
አቶ ምትኩ ሄርጳ እባላለሁ፡፡ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የፅዳት አስተዳደር ኤጀንሲ የግንዛቤ ስርፀት፣ የህብረተሰብ ተሳትፎ የአካባቢ ንፅህና ክትትል ዳይሬክተር ነኝ፡፡ ልጆች እጃችሁን፣ ፊታችሁን፣ እግራችሁን፣ ሰውነታችሁን፣ ፀጉራችሁን በመታጠብ፣ ጥርሳችሁን በመቦረሽ እና ንፁህ ልብስ በመልበስ የግል ንፅህናችሁን ትጠብቃላችሁ አይደል? ጎበዞች፡፡ የግል ንፅህናቸሁን እንዲህ ከጠበቃችሁ የምትውሉበትንና የምትኖሩበትን አካባቢ በንፅህና መያዝንም እንዳትዘነጉ፡፡ ይህን የምታደርጉት የምትማሩባቸውንና የምትጫወቱባቸውን ቁሳቁስ በአግባቡ በማስቀመጥ፣ የከረሜላና ብስኩት ወረቀት፣ የፍራፍሬ ልጣጭ፣ የተጠቀማችሁበትን ሃይላንድ እና የመሳሰሉትን ቆሻሻ በአግባቡ የቆሻሻ መጣያ ውስጥ በመጣል ነው፡፡
ልጆች፤ የራሳችሁንም ሆነ የአካባቢያችሁን ንፅህና መጠበቃችሁ ጤናችሁ የተጠበቀ እንዲሆን ያደርጋል፡፡ አካባቢያችሁም ሆነ ከተማችሁ ለእይታ ማራኪ ይሆናሉ፡፡ ስለዚህ ቆሻሻን በቆሻሻ መጣያ ቅርጫት ውስጥ ማስወገድ፣ የትምህርት ቤት አካባቢያችሁን አርብ አርብ በሚኖረው መርሃ ግብር ላይ በመሳተፍ ማፅዳት አለባችሁ፡፡ በንፁህ አካባቢ የመማር መብት እንዳላችሁ ሁሉ የአካባቢያችሁን፣ የትምህርት ቤታችሁን እንዲሁም የከተማችሁን ንፅህና የመጠበቅ ኃላፊነትም አለባችሁ፡፡
በፋንታነሽ ተፈራ