አዲስ አበባ የአፍሪካ የጤና ቱሪዝም ማዕከል የመሆን አቅሟን በተግባር እያሳየች ነው

AMN – ነሐሴ 24/2018 ዓ.ም

አዲስ አበባን የጤና ቱሪዝም ማዕከል የማድረግ ራዕይን በመሰነቅ፣ ባለፉት አምስት ዓመታት በተከናወኑ ሥራዎች የሕክምና አገልግሎት ጥራትና የተደራሽነት አቅም ከእጥፍ በላይ እንዲያድግ ተደርጓል።

መዲናዋ ባስመዘገበችው ሁለንተናዊ ዕድገት የአህጉሪቱ የዲፕሎማሲ፣ የንግድ እና የኮንፈረንስ ማዕከልነቷን ከማጠናከሯ ባሻገር፣ የጤና ቱሪዝም መዳረሻ የመሆን አቅሟን በተግባር እያሳየች ትገኛለች።

ሀገራዊ ለውጡን ተከትሎ የከተማ አስተዳደሩ ባከናወናቸው ተግባራት፣ በሰው ሰራሽ አስተውሎት እና በዘመናዊ የሕክምና ቴክኖሎጂ የታገዙ እንዲሁም የላቁ ባለሙያዎችን ያቀፉ ግዙፍ ሆስፒታሎችና ጤና ተቋማት ተገንብተው ለአገልግሎት በቅተዋል።

በተቋማቱ የተዘረጉት የዲጂታል አሠራሮች፣ ዘመናዊ የቀዶ ሕክምና እና አውቶሜትድ የላብራቶሪ መሣሪያዎች ታካሚዎች ጥራት ያለው አገልግሎት እንዲያኙ ዕድል የፈጠሩ ናቸው።

እነዚህ የላቀ ደረጃ ያላቸው የጤና ተቋማት በመዲናዋ መገንባታቸው፣ ቀደም ሲል ዜጎች ለከፍተኛ ሕክምና ወደ ውጭ ሀገር የሚያደርጉትን ጉዞ በመቀነስ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪን ማዳን የሚያስችል ነው።

የጤና ተቋማቱ ዘመናዊ የቆሻሻ አወጋገድ ሥርዓታቸው ከአካባቢ ጥበቃ እና ከአረንጓዴ ልማት ሥራዎች ጋር ተጣጥሞ የተገነባ ነው።

ለእነዚህ ስኬቶች የከተማዋ የሃያ አራት ሰዓት (24/7) የሥራ ባህል፣ የአመራሩ ቁርጠኝነት እና የነዋሪዎች ትብብር ዋነኛ መሠረት ናቸው።

የሕክምና ጥራቱን አሁን ካለበት ደረጃ በማሳደግ፣ ለከፍተኛ ሕክምና ወደ ተለያዩ የዓለም ክፍሎች የሚጓዙ አፍሪካውያንን ወደ አዲስ አበባ በመሳብ ከተማዋን ተመራጭ የሕክምና መዳረሻ እንደሚያደርጋት ታምኖበታል።

በወርቅነህ አቢዮ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review