AMN- ነሐሴ 25/2018 ዓ.ም
አዲስ አበባ በደቡብ ምስራቅ እስያና በአፍሪካ መካከል ዋና የትስስር ድልድይ ሆና እያገለገለች ነው ሲሉ የታይላንድ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሲሃሳክ ፉአንግኬትኪኦ ገለጹ፡፡
ታይላንድ ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን ስትራቴጂካዊ ትብብር ለማጠናከር እና ከአፍሪካ አህጉር ጋር ያላትን አጋርነት ለማስፋት ፍላጎት እንዳላትም አስታውቀዋል፡፡
የታይላንድ የውጭ ጉዳይ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ሲሃሳክ ፉአንግኬትኪኦ በኢትዮጵያ ይፋዊ የሥራ ጉብኝት አድርገዋል።
የጉብኝታቸው ዋና ዓላማም ከኢትዮጵያ ጋር ያለውን ታሪካዊ የሁለትዮሽ ግንኙነት ማጠናከር እና መቀመጫነቱ አዲስ አበባ ከሆነው የአፍሪካ ኅብረት ጋር ያለውን ተሳትፎ ማሳደግ እንደሆነ አብራርተዋል።
ኢትዮጵያ ከታይላንድ ጋር የቆየ ታሪካዊ ግንኙነት ያላት ሀገር መሆኗን አንስተው፤ ሀገራቸው ይህንን ግንኙነት ይበልጥ ለማጠናከር እና ሁለንተናዊ ትብብሯን ለማሳደግ እንደምትሠራ አስታውቀዋል።
በተለይም በኢንዱስትሪ ልማት እና በግብርና ምርቶች ላይ እሴት በመጨመር ረገድ ያላትን መልካም የልማት ተሞክሮ ለኢትዮጵያ ለማካፈል ዝግጁ መሆኗን ገልጸዋል።
አዲስ አበባ በደቡብ ምስራቅ እስያ እና በአፍሪካ መካከል ዋና የትስስር ድልድይ ሆና እየወጣች መሆኗን ተናግረዋል። በዚህም ታይላንድ በአዲስ አበባ ኤምባሲዋን ለመክፈት መወሰኗን ጠቁመዋል፡፡
ሀገራቸው በአፍሪካ ያላትን ዲፕሎማሲያዊ ተጽዕኖ ለማጠናከር እና አዲስ አበባን የመላው አህጉራዊ ግንኙነቷ ዋና ማዕከል ለማድረግ የምታደርገውን ጥረት የሚያሳይ መሆኑን ጠቅሰዋል።

አዲስ አበባ የአሴአን (ASEAN) እና የአፍሪካ ዋና የትስስር ማዕከል መሆኗን የጠቆሙት ዲፕሎማቱ፤ ኢትዮጵያና ታይላንድ በአፍሪካ ኅብረትና በአሴአን መካከል ጠንካራ የትብብር ድልድይ በመገንባት ከፍተኛ ሚና መጫወት እንደሚችሉ መግለጻቸውን ኢዜአ ዘግቧል።
ሚኒስትሩ ታይላንድ እና የአፍሪካ ሀገራት ሕግን መሠረት ያደረገውን ዓለም አቀፍ ሥርዓት ለማስጠበቅ፣ ነፃ ንግድን ለማስቀጠል እና በዓለም የንግድ ድርጅት (WTO) ሥር ያለውን የንግድ ሥርዓት ለማጠናከር በጋራ መሥራት እንዳለባቸው አሳስበዋል።
የኢትዮጵያ የዓለም ንግድ ድርጅት አባል መሆንም ከዓለም አቀፍ የንግድ ሕጎች እና ኢኮኖሚ ጋር በንቃት እንድትሳተፍ የሚያበረታታ መሆኑን አብራርተዋል።