AMN-ነሐሴ 24/2018 ዓ.ም
የእንግሊዝ ፕሪምየር ሊግ ሁለተኛ ሳምንት መርሃግብር ጨዋታዎች ዛሬም ሲቀጥሉ ማንችስተር ዩናይትድ ከአንድ ዓመት በኋላ ወደ ሊጉ የተመለሰው ኢፕስዊች ታውንን ይገጥማል።
በአዲስ አዳጊው ሃል ሲቲ ተሸንፎ የጀመረው ዩናይትድ የውድድር ዓመቱን የመጀመሪያ ድል ለማግኘት ይፋለማል።
በኦልድትራፎርድ በሚከናወነው ጨዋታ በዩናይትድ በኩል ሜሰን ማውንት ወደ ስብስቡ ይመለሳል ተብሎ ይጠበቃል። ማይክል ካሪክ ከአስደንጋጩ የሀል ሲቲ ሽንፈት በኋላ በመጀመሪያ አሰላለፉ ላይ ለውጥ ሊያሳይ እንደሚችል ተገምቷል።
ሰንደርላንድን አሸንፎ የውድድር ዓመቱን የጀመረው ኢፕስዊች ታውን ግን ቀላል ተጋጣሚ ይሆናል ተብሎ አይጠበቀም።
ዩናይትድ ከኢፕስዊች ጋር በኦልድትራፎርድ ባደረጋቸው ስምንት የመጨረሻ የሊግ ጨዋታዎች ሽንፈት አልገጠመውም። ስድስቱን አሸንፎ በሁለቱ አቻ ተለያይቷል።
ዩናይትድ ዛሬ ምሽት 12:30 በሚጀምረው ጨዋታ አዲስ ፈራሚው ካርሎስ ባሌባን ለደጋፊዎቹ ያስተዋውቃል ተብሏል።
ቼልሲ ከ ብራይተን ፣ ሊድስ ዩናይትድ ከ ብሬንትፎርድ እንዲሁም ሰንደርላንድ ከ ፉልሃም ሌሎች ዛሬ የሚከናወኑ ጨዋታዎች ናቸው። ሦስቱም ጨዋታዎች በተመሳሳይ 10:00 ላይ ይጀምራሉ።
በሸዋንግዛው ግርማ