AMN – መጋቢት 21/2018 ዓ.ም
የሳይንስ ሊቃውንት እንደሚናገሩት፣ የአንድ ሕፃን አእምሮ 85 በመቶ የሚሆነው የሚገነባው እስከ አምስት ዓመት ዕድሜ ባለው የዕድሜ ክልል ነው። ለዚህ ደግሞ ሕፃናት በነፃነት የሚንቀሳቀሱበትና ከአካባቢያቸው ጋር የሚገናኙበት ምቹ ስፍራ ያስፈልጋቸዋል። ባለፉት 12 ወራት የተገነቡት የኮሪደር ልማቶች ደግሞ ይህንን ሳይንሳዊ እውነት ታሳቢ ያደረጉ ናቸው።
በየኮሪደሩ የተካተቱት ሰፋፊ መናፈሻዎች፣ ከትራፊክ አደጋ የጸዱ የእግረኛ መንገዶች እና በየመሃሉ የተሰሩ ትንንሽ የሕፃናት መጫወቻ ስፍራዎች ከቀዳማይ ዕድሜ ጀምሮ ላሉ ልጆችና ታዳጊዎች አዲስ ዓለም ፈጥረዋል። ዛሬ የልጆች የደስታ ምንጭ የሆኑትን እነዚህን ስፍራዎች አዲስ አበባ ውስጥ ዕውን ማድረግ ከዓመታት በፊት ሊታሰብ የማይችል ከባድ ነገር ነበር።
አሁን ግን አዲስ አበባ በጭስና በጩኸት የተሞላች ከመሆን ወጥታ እንዲሁም ወላጆችም ሕፃናትን ይዘው በጠባብ መንገድ ላይ እየተሳቀቁ ከመንቀሳቀስ ስጋት ወጥተው ለእነርሱም ለልጆቻቸውም አዲስ ዓለም ተፈጥሯል።

ካለፈው መጋቢት እስከዘንድሮው መጋቢት ድረስ አዲስ አበባ ምን ያህል ለሕፃናት የምትመች ከተማ እንደሆነች ለተመለከተ የአዲስ አበባን ለውጥ በተግባር መረዳት አያዳግተውም። ለዚህም ነው የአዲስ አበባ ከንቲባ አዳነች አቤቤ “አዲስ አበባ ከተማ ሕፃናትን ለማሳደግ የምትመች ምርጧ አፍሪካዊት ከተማ እናደርጋታለን” ያሉት።
ባለፈው አንድ ዓመት ውስጥ በከተማዋ የተገነቡት ዘመናዊ የሕዝብ መጸዳጃ ቤቶች እና በየቦታው የተቀመጡ የቆሻሻ ማጠራቀሚያዎችም ቢሆኑ ሕፃናት ከበሽታ ነፃ በሆነ አካባቢ እንዲያድጉ ትልቅ አስተዋጽዖ አበርክተዋል።
በተለይም በወንዝ ዳርቻዎች የተሰሩት የልማት ስራዎች፣ ቀደም ሲል ለሕፃናት ጤና ጠንቅ የነበሩትን ስፍራዎች ወደ ንጹህ አየር ምንጭነት ቀይረዋቸዋል። ይህ ለውጥ ሕፃናት በተፈጥሮ መካከል ሆነው እንዲማሩ እና እንዲመራመሩ ዕድል ፈጥሯል። በየመንገዱ ዳር የተሰሩት የንባብ ማዕከላትና ጥበባዊ ቅርጻ ቅርጾች፣ ሕፃናት ገና በለጋነታቸው ለጥበብና ለንባብ ፍቅር እንዲኖራቸው የሚገፋፉ መሆን ችለዋል።

የከተማ አስተዳደሩ በየክፍለ ከተማው የገነባቸው የሕፃናት ማቆያ ማዕከላት ደግሞ ዝቅተኛ ገቢ ያላቸው እናቶች ልጆቻቸውን በአስተማማኝ ቦታ አሳርፈው ወደ ስራ እንዲሰማሩ በማድረግ፣ ለቀዳማይ ልጅነት ዕድገት ስር ነቀል ለውጥ አምጥቷል።
የኮሪደር ልማቱ ድንጋይና አስፋልት ብቻ ሳይሆን፣ የነገው ትውልድ ሥነ-ልቦና የሚቀረጽበት “ክፍት ትምህርት ቤት” ሆኗል።
ዛሬ በእነዚህ መንገዶች ላይ የሚሮጡት ሕፃናት፣ ነገ በሥነ-ምግባርና በዕውቀት የበለጸገች ኢትዮጵያን የሚገነቡ ዜጎች ለመሆናቸው እነዚህ የ12 ወራት ስራዎች ትልቅ ዋስትና ናቸው።
አዲስ አበባ አሁን መዲና ብቻ አይደለችም፤ ለሕፃናት የምትመች፣ የምታቅፍ እና የምታሳድግ “ሞግዚት” ከተማም ሆናለች።
በሀበነዮም ሲሳይ