የኢትዮጵያ ቱሪዝም ሽግግር

You are currently viewing የኢትዮጵያ ቱሪዝም ሽግግር

AMN- መጋበት 22/2018 ዓ.ም

ኢትዮጵያ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በብዝሃ ኢኮኖሚ ግንባታ በትኩረት እየሰራችባቸው ካሉ ዘርፎች መካከል አንዱ ቱሪዝም ነው።

ባለፉት ስምንት ዓመታት በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) አነሳሽነት በቱሪዝም ዘርፉ በተከናወኑ መጠነ ሰፊ ሪፎርሞች ከነባር የቱሪስት መዳረሻዎች እድሳት ባለፈ ገበታ ለሸገር፣ ገበታ ለሀገር እና ገበታ ለትውልድ መርሀ ግብርን በመቅረጽ የኢትዮጵያ የቱሪስት መዳረሻነት ከፍተኛ መሻሻል አሳይቷል፡፡ ዘርፉ ቀደም ሲል ከነበረበት የባህልና የታሪክ መዳረሻነት ባለፈ፣ የሀገሪቱን ገጽታ የሚቀይሩና ለኢኮኖሚው ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬና የሥራ ዕድል የሚፈጥሩ ዘመናዊ ፕሮጀክቶች ተተግብረውበታል።

የቱሪዝም ልማት ገበታ ለሸገር፣ ለሀገር እና ለትውልድ መርሃ-ግብሮች የኢትዮጵያን የተፈጥሮና ሰው ሰራሽ ፀጋዎች ወደ ኢኮኖሚያዊ ጥቅም ለመቀየር የታለሙ ታሪክ ቀያሪ ስራዎች ናቸው።

የአዲስ አበባን ገጽታ በመቀየር ረገድ ትልቅ ድርሻ የነበረው ገበታ ለሸገር መርሃ-ግብር እንደ አንድነት ፓርክ፣ የወዳጅነት ፓርክ እና የእንጦጦ ፓርክ የመሳሰሉ ግዙፍ መዳረሻዎችን አስገኝቷል።

መንግስት በገበታ ለሀገር ትኩረቱን በክልሎች ላይ በማድረግ በደቡብ ኢትዮጵያ ሀላላ ኬላ እና ጨበራ ጩርጩራ ፣ በኦሮሚያ ወንጪ እንዲሁም በአማራ ክልል ጎርጎራ ላይ ዓለም አቀፍ ደረጃቸውን የጠበቁ ሪዞርቶችና መሠረተ ልማቶች እንዲገነቡ አስችሏል።

በቅርቡ የተጀመረውና በሦስተኛው ምዕራፍ ገበታ ለትውልድ መርሃ-ግብር በመላ ሀገሪቱ ለትውልድ ኩራትና ቅርስ የሚሆኑ የቱሪስት መስህቦችን በማልማት ላይ ይገኛል። በዚህም በተያዘው በጀት አመት ግንባታቸው ተጠናቆ የተመረቁት የሸበሌ ሪዞርት፣ የሎጎ ሐይቅ ሪዞርት፣ ሶርጋ ኢኮ ሎጅ እና ኒዒን ሌ ፓልም ሎጅ ተጠቃሽ ናቸው።

በሌላ በኩል ባለፉት ስምንት አመታት አዲስ አበባ የዓለም የዲፕሎማሲ ማዕከልነት ተከትሎ በኮንፍረንስ ቱሪዝም መዳረሻነት ረገድ ከፍተኛ መሻሻል ታይቷል። በመዲናዋ የተገነቡት የአድዋ እና የሳይንስ ሙዚየም እንዲሁም አዲስ ኮንቬንሽን ማዕከል ፕሮጀክቶች አዲስ አበባን የኮንፍረንስና የቱሪዝም ማዕከል አድርገዋታል።

ባለፉት ስድስት ወራት ብቻ በመዲናዋ ከ150 በላይ ዓለም አቀፍ ጉባኤዎች በስኬት ተካሂደዋል፡፡ ይህም የቱሪስት ፍሰቱ በመጨመርና የቆይታ ጊዜያቸው በመራዘም ለሀገሪቱ የውጭ ምንዛሬ ገቢ ዕድገት ትልቅ አስተዋጽኦ አድርጓል።

በለውጡ መንግስት ለቱሪዝም የተሰጠው ልዩ ትኩረት ኢኮኖሚያዊ ፋይዳው ዘርፈ ብዙ ሲሆን በእነዚህ ፕሮጀክቶች ግንባታና አገልግሎት አሰጣጥ ወቅት ለብዙ ሺህ ዜጎች በተለይም ለወጣቶች የሥራ ዕድል ተፈጥሯል።

ባለፉት ስምንት የለውጥ እና የብልጽግና ዓመታት የተከናወኑት የቱሪዝም ልማት ሥራዎች ኢትዮጵያን ከአፍሪካ አልፎ በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ የቱሪዝም ማዕከል ለማድረግ የተቀመጠውን ራዕይ ስኬታማነት እያረጋገጠ ነው፡፡

በትዝታ መንግስቱ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review