AMN – መጋቢት 23/2018 ዓ.ም
በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የጂኦግራፊ፣ የአካባቢ ጥናት ትምህርት ክፍል መምህር እና ተመራማሪ እንዲሁም የከተማ ፕላን (Urban Planning) ባለሙያው ፣ ፕሮፌሰር ሰለሞን ሙሉጌታ የኢትዮጵያ የወደፊት ብልጽግና ከከተሞች እድገትና ከዘመናዊ የከተማና ገጠር ትስስር ጋር በቀጥታ የተቆራኘ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
ፕሮፌሰሩ አዲስ አበባን ጨምሮ በሀገሪቱ እየተከናወኑ ያሉ የኮሪደር ልማት ስራዎች፣ የሜጋ ፕሮጀክቶች፣ የዲጂታል መሰረተ ልማት ትራንስፎርሜሽን እና ቀጣናዎችን በልማት የማስተሳሰር ስራ ያላቸውን የጎላ ፋይዳ አስረድተዋል።
ከተማነት በአግባቡ ሲመራ ለሀገር ኢኮኖሚ እድገትና ለዜጎች ሁለንተናዊ ብልጽግና እንደ ትልቅ ሞተር እንደሚያገለግል ፕሮፌሰር ሰለሞን ሙሉጌታ አስገንዝበዋል፡፡
ከተማ በአግባቡ ገጠሩን ማገልገል ሲችል የተቀናጀ ሀገራዊ እድገት ይመጣል ያሉት ፕሮፌሰሩ፣ ማንኛውም ከተማ በዙሪያው በቀጥታ የሚያገለግለውና የሚገለገልበት የራሱ የሆነ አካባቢ እንዳለው ጠቅሰዋል፡፡
ከተማው እንደ የንግድ አሳላጭ በመሆን ከገጠር ምርትን ሰብስቦ ለአገር ዉስጥና ለውጭ ገበያ ያቀርባል፤ በተቃራኒው ደግሞ ከአገር ዉስጥና ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን ለገጠሩና በዙሪያው ለሚገኙ ትላልቅ እና ትናንሽ ከተሞች እንደሚያከፋፍልም አስረድተዋል፡፡
አንድ ከተማ በትራንስፖርትና በመሰረተ ልማት ከገጠሩ አካባቢ ጋር በአግባቡ ካልተሳሰረ ሁለቱም የሚኖራቸው ግንኙነት የተገደበ እንደሚሆን አስገንዝበዋል።
በአሁኑ ወቅት ከ6 ሚሊዮን በላይ የህዝብ ቁጥር እንዳላት የምትገመተው አዲስ አበባ ከተማ ከሌሎች ብዙ የህዝብ ቁጥር ይኖርባቸዋል ከሚባሉት እንደ ከአዳማ፣ ድሬ ዳዋ፣ ጎንደርና ባህርዳር ከመሰሉት ትላልቅ ከተሞች በብዙ እጥፍ በመግዘፍ ፖለቲካውንና ኢኮኖሚውን በብቸኝነት የምትቆጣጠር ከተማ መሆኗን ፕሮፌሰሩ ለአብነት ገልጸዋል፡፡
ይህም ክስተት ሁሉንም እንቁላሎች በአንድ ቅርጫት የመጨመር ያህል አደገኛ ሊሆን እንደሚችልም አመላክተዋል
ይሁን እንጂ የፌደራል ስርዓቱ ከተዘረጋ በኋላ በአገሪቱ ዙሪያ ያሉ ብዙ ትላልቅ፣ መካከለኛ እና ትናንሽ ከተሞች በፍጥነት አድገዋል ያሉት ፕሮፌሰሩ፣ እንደ ወራቤ ያሉ ትናንሽ ከተሞች እንኩዋን ወደ ዩኒቨርሲቲ ከተማነት ማደጋቸው ተስፋ ሰጪ መሆኑን ጠቅሰዋል።
ባገራችን ብዙ ሰዎች ከገጠር ወደ ከተማ የሚደረገውን የህዝብ ፍልሰት ቁጥጥር ሊደረግበት እንደሚገባው ጎጂ ነገር አድርገው ያዩታል ያሉት ፕሮፌሰር ሰለሞን፣ ፍልሰት እንደማይቆም እና መቆምም እንደሌለበት አንስተው፤ የከተሞች መብዛትና ማደግ ከጉዳቱ ይልቅ ጥቅሙ በእጅጉ እንድሚበልጥ አስምርዉበታል።
ይህንኑ ሃሳብ ሲያብራሩም ለምሳሌ አሉ ፕሮፌሰሩ፣ ወጣቶች ወደ ከተማ ገብተው በዝቅተኛ ገቢ ስራ ጀምረው በሂደት ሀብት ሲያፈሩ ተመልሰው ገጠሩን እንደሚረዱና ይህም ሂደት ግብርናው በቴክኖሎጂ እንዲታገዝ መንገድ እንደሚከፍት አስረድተዋል።
ፕሮፌሰር ሰለሞን አክለውም የከተማ ነዋሪ ህዝብ ብዛት በፐርሰንት ሲሰላ አገሩ የደረሰበትን የኤኮኖሚ እድገት ደረጃ የሚያሳይ ዓለም አቀፍ መስፈርት መሆኑንም ጠቅሰዋል፡፡
የብዙ ታዳጊ አገሮች ልምድ እንደሚያሳየው የአንድ ከተማ ነዋሪ ህዝብ ብዛት በፐርስንት ሲሰላ ከ45 እስከ 50 በመቶ ሲደርስ ወይም ከዚያ አለፍ ሲል እነዚያ አገሮች ግልጽና አመርቂ የሆነ የኢኮኖሚ እድገት መንደርደርና መነሳሳት ላይ መሆናቸውን ያሳያል ብለዋል፡፡
በአሁኑ ወቅት የከተማ ነዋሪ የሆነው የኢትዮጵያ ህዝብ በግምት ከ23 በመቶው አይበልጥም ያሉት ፕሮፌሰሩ፣ አዲስ አበባ ከተማ ብቻዋን ከ20 እስከ 22 በመቶውን የምትይዝ ስትሆን፣ የሀገሪቱን 30 በመቶ GDP ወይም የሀገር ውስጥ ጠቅላላ ምርት እንደምትሸፍንም አብራርተዋል፡፡
ለአንድ ከተማ ማደግና መዘመን ማሳያው በከተማዋ ውስጥ የሚሰጠው የተሟላ አገልግሎት አሰጣጥን እና መሰረተ ልማት መሟላት መሆናቸውን ያነሱት ፕሮፌሰሩ፣ አዲስ እየተገነባ ያለው የቢሾፍቱ አውሮፕላን ማረፊያ፣ የዲጂታል ግብር አከፋፈል፣ የአንድ ማዕከል የመሶብ አገልግሎት እና የወንዞች ዳርቻ ልማት አዲስ አበባ ከተማን ለዓለም አቀፍ ባለሀብቶች ምቹ እንደሚያደርጓትም ገልጸዋል።

በአዲስ አበባ ከተማ እና በሌሎችም ከተሞች በመከናወን ላይ ያለው እና ወደ ገጠሩም እየተስፋፋ በሚገኘው የኮሪደር ልማት ለበርካታ ወጣቶች የስራ እድል መፍጠር መቻሉ ጠቅሰዋል።
በአዲስ አበባ የወንዞች ዳርቻ ልማት ላይ እየተከናወኑ ባሉ የእርከን ስራዎች አገር በቀል የሆነው እውቀትን በመጠቀም በተለይም የኮንሶን የእርከን ጥበብ በመዲናዋ የልማት ስራ ላይ በማሳተፍ በከተሞችና በገጠር መካከል ያለውን የልማትና የእድገት ትስስር ማሳያ መሆኑን ፕሮፌሰሩ በማድነቅ ገልጸዋል፡፡
በወርቅነህ አቢዮ