መጋቢት- በኢትዮጵያ የሴቶች ወደ ከፍተኛ አመራርነት መምጣት የተበሰረበት ወር

You are currently viewing መጋቢት- በኢትዮጵያ የሴቶች ወደ ከፍተኛ አመራርነት መምጣት የተበሰረበት ወር

AMN- መጋቢት 23/2018 ዓ.ም

ባለፉት የለውጥ ዓመታት በኢትዮጵያ ፖለቲካዊ ምህዳር ውስጥ ከተመዘገቡ ተጨባጭ ድሎች መካከል የሴቶች በከፍተኛ የሥልጣን እርከን ላይ የመሳተፍ ጉዳይ በቀዳሚነት የሚጠቀስ ነው።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የሴቶች ውሳኔ ሰጪነት ሚና እንዲጎለብትና የሴት አመራር ቁጥር እንደሚሻሻል ገና ወደ ስልጣን ሲመጡ ቃል የገቡት ቀዳሚ አጀንዳቸው ነበር፡፡

መንግስት የወሰደው ቁርጠኝነት የታየበት የካቢኔ ስብጥር ማሻሻያ ኢትዮጵያን በዓለም አቀፍ ደረጃ በጾታ እኩልነት ስኬታማ ከሆኑ ጥቂት ሀገራት ተርታ እንድትመደብ አስችሏታል።

ይህ ለውጥ ቀደም ሲል ሴቶች ይመደቡባቸው ከነበሩ የማህበራዊ ዘርፎችም በማለፍ እንደ ሀገር መከላከያ፣ሰላም ሚኒስቴር፣ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ እና የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤትን የመሳሰሉ ስልታዊና ወሳኝ ተቋማትን በሴት አመራሮች እንዲመሩ በማድረግ አዲስ ደማቅ ታሪክ ጽፏል።

በተለይም በሀገሪቱ ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ ሴት ፕሬዚዳንት ተሹመው ሀገሪቱን በዓለም አቀፍ መድረክ መወከላቸው ለሴት ልጆች ትልቅ ተስፋንና የሥነ-ልቦና ጥንካሬን የፈጠረ ተምሳሌታዊ እርምጃ ሆኖ ተመዝግቧል።

ከሹመት ባለፈ በሕግና በፖሊሲ ረገድ የተከናወኑ ማሻሻያዎች የሴቶችን ተሳትፎ መዋቅራዊ መሠረት እንዲይዝ አድርገውታል።

በሲቪል ሰርቪስና በምርጫ ሕጉ ላይ የተደረጉ ማሻሻያዎች የሴቶች የውሳኔ ሰጪነት ሚና እንዲያድግ ምቹ ሁኔታን የፈጠረ ሲሆን፣ ይህ አካታች አሠራር የመንግስት ውሳኔዎች ሁሉንም የህብረተሰብ ክፍል ያገናዘቡ እንዲሆኑ ከማድረጉም በላይ የሀገሪቱን ዲፕሎማሲያዊ ገጽታ በመገንባት ረገድ ከፍተኛ ፋይዳ አስገኝቷል።

ከመጋቢት እስከ መጋቢት በተደረገው የለውጥ ጉዞ፣ በከፍተኛ አመራር ደረጃ የታየው ለውጥ ለወደፊቱ ጠንካራ መሠረት የጣለና የሴቶችን የአመራር ብቃት በተግባር ያስመሰከረ መሆኑን ቃል በተግባር ተደግሞበታል፡፡

በሚካኤል ህሩይ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review