በሀገራዊ ለውጡ- የዲጂታል እምርታ

You are currently viewing በሀገራዊ ለውጡ- የዲጂታል እምርታ

AMN- መጋቢት 23/2018 ዓ.ም

ከሀገራዊ ለውጡ ወዲህ በኢትዮጵያ የታየው የዲጂታል እድገት አገሪቱ ከነበረችበት ዝግ የቴክኖሎጂ ሥርዓት ወደ ዲጂታል ኢኮኖሚ ለመሸጋገር ላደረገችው ጥረት ማሳያ ነው፡፡

ይህን ጥረት ለማሳካትም በመጀመሪያ መንግሥት “ዲጂታል ኢትዮጵያ 2025” የተሰኘ ስትራቴጂ ቀርጾ ተንቀሷል፡፡

ቀጥሎም መንግስት ዲጂታል ኢትዮጵያ 2030 ስትራቴጂን የቀረፀ ሲሆን ይህም የቀድሞውን የ”ዲጂታል 2025″ ስትራቴጂ ስኬቶች መሠረት በማድረግ፣ አገሪቱን ወደ ላቀ የቴክኖሎጂ ምዕራፍ ለማሸጋገር ታኅሣሥ 11 ቀን 2018 ዓ.ም በይፋ የተጀመረው አዲስ አገራዊ ራዕይ ነው።

ይህ ስትራቴጂ ኢትዮጵያን በ2030 የበለፀገችና በቴክኖሎጂ የዳበረች ለማድረግ ያቀዳቸው ዲጂታል አገልግሎቶች ለከተማ ብቻ ሳይሆን ለገጠሩም ማኅበረሰብ እኩል ተደራሽ እንዲሆኑ ማድረግን ያለመ ስትራሬጂ ነው፡፡

ሌላኛው በኢትዮጵያ የአርቴፊሻል ኢንተለጀንስ (AI) ጉዞ ካለፉት አምስት ዓመታት ወዲህ ትልቅ ትኩረት ተሰጥቶት እየተንቀሳቀሰ ያለ ዘርፍ ነው።

አገሪቱ ቴክኖሎጂውን ለልማትና ለኢኮኖሚ ዕድገት ለመጠቀም በርካታ ተቋማዊና ፖሊሲ ነክ እርምጃዎችን እየወሰደች ትገኛለች።

የ5 ሚሊዮን ኮደርስ ኢንሼቲቭ ኢትዮጵያውያን ወጣቶችን በዲጂታል ክህሎት በተለይም በኢትዮጵያ የአርቴፊሻል ኢንተለጀንስ (AI) ላይ ለማሰልጠን ያለመ ነው። ይህ ለዘርፉ የሚያስፈልገውን የሰው ኃይል ለማፍራት እንደ ትልቅ መሠረት ይታያል።

ለበርካታ ዓመታት በመንግሥት ቁጥጥር ስር የነበረውን የቴሌኮም ዘርፍ ለውጭ ውድድር ክፍት በማድረግ “ሳፋሪ ኮም ኢትዮጵያ” ወደ ገበያ እንዲገባ ሆኗል። ይህም የኢንተርኔት ተደራሽነትንና ጥራትን እንዲሻሻል አድርጓል።

የኤሌክትሮኒክ ግብይት አዋጅ በተመለከተም፣ የዲጂታል ክፍያና የኢ-ኮሜርስ (E-commerce) ሕጋዊ እውቅና እንዲያገኙ በማድረግ የንግድ ሥርዓቱን ዘመናዊ ለማድረግ መንገድ ከፍቷል።

የብሔራዊ ዲጂታል መታወቂያ ተግባራዊ እንዲሆን መደረጉ ዜጎችን በዲጂታል ሥርዓት ለመመዝገብና ማጭበርበርን ለመቀነስ የሚረዳው ይህ ፕሮጀክት ለፋይናንስና ለሌሎች አገልግሎቶች መሠረት እየሆነ ነው።

የክፍያ ሥርዓት ዘመናዊነት ለማዘመን የ”ቴሌብር” መጀመርና የባንኮች የዲጂታል ባንኪንግ መስፋፋት የገንዘብ ዝውውርን ከወረቀት ወደ ስልክ ቀይሮታል። ይህም በተለይ ለጥቃቅንና አነስተኛ ንግዶች ትልቅ ዕድል ፈጥሯል።

እንዲሁም የመንግሥት አገልግሎቶች በዲጂታል በማድረግ ፓስፖርት ማውጣት፣ የንግድ ፈቃድ ማደስና የታክስ ክፍያዎች አሁን ላይ በከፊልም ቢሆን በኦንላይን እንዲከናወኑ መደረጉ ቀልጣፋ አገልግሎት እንዲኖር ረድቷል።

የሳይንስና ቴክኖሎጂ ሙዚየም በአዲስ አበባ የተገነባው የሳይንስ ሙዚየም ለወጣቶች የፈጠራ ሥራ ማበረታቻና የቴክኖሎጂ ማዕከል ሆኖ እያገለገለ ይገኛል።

የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር (INSA) ዳግም መደራጀት የአገሪቱን የዲጂታል ሉዓላዊነት ለመጠበቅና የሳይበር ደህንነትን ለማረጋገጥ ተቋማዊ አቅምን የማሳደግ ሥራ ተሠርቷል።

ባጠቃላይ ባለፉት ጥቂት ዓመታት የተመዘገቡት ስኬቶች ኢትዮጵያ ወደ ዲጂታል ዓለም ለመግባት ያላትን ቁርጠኝነት የሚያሳዩ ቢሆንም፣ የኢንተርኔት ነፃነትን ማረጋገጥና መሠረተ-ልማቱን አስተማማኝ ማድረግ ለወደፊቱ ስኬት ወሳኝ ናቸው።

በቶለሳ መብራቴ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review