አየር መንገዱ ለበረራ መቆጣጠሪያ የሚያገለግሉ ቁሶችን በማምረት ለውጭ ገበያ እያቀረበ ነው

You are currently viewing አየር መንገዱ ለበረራ መቆጣጠሪያ የሚያገለግሉ ቁሶችን በማምረት ለውጭ ገበያ እያቀረበ ነው

AMN- መጋቢት 24/2018 ዓ.ም

የኢትዮጵያ አየር መንገድ፣ ሁሉንም አውሮፕላን በራሱ አቅም ከመጠገን ባለፈ፣ ለሌሎች ሀገራትም አገልግሎት በመስጠት አድማሱን እያሰፋ እንደሚገኝ ገለጸ፡፡

ለአውሮፕላን በረራ መቆጣጠሪያ የሚያገለግሉ ኬብሎችን በማምረት ለውጭ ገበያ እያቀረበ መሆኑን አየር መንገዱ አስታውቋል፡፡

የኢትዮጵያ አየር መንገድ በአውሮፕላን ጥገና፣ እድሳት እና አጠቃላይ ምርመራ (MRO) ዘርፍ በአፍሪካ ያለውን ቀዳሚነት የሚያሳይ ዓለም አቀፍ ኮንፈረንስ ባለፉት 3 ቀናት በአዲስ አበባ አካሂዷል።

ከ40 በላይ የአፍሪካ ሀገራት እና የዓለም አቀፍ ኩባንያዎች በተሳተፉበት በዚህ መድረክ፣ አየር መንገዱ የራሱን አውሮፕላኖች ከመጠገን አልፎ ለታዋቂው የቦይንግ ኩባንያ የአውሮፕላን መለዋወጫ ግብዓቶችን እያመረተ ማቅረብ መጀመሩ ተገለጿል።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ መስፍን ጣሰው፣ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ሁሉንም አይነት አውሮፕላኖች በራሱ አቅም መጠገን የሚችል በአህጉሪቱ ብቸኛው እና ትልቁ የአውሮፕላን ጥገና ማዕከል እና ባለቤት መሆኑን ተናገረዋል።

ዋና ሥራ አስፍጻሚው አክለው ይህን መድረክ አየርመንገዱን ይበልጥ ለማስተውወቅ እንደተጠቀሙበትም ጠቁመዋል።

የኢትዮጵያ አየርመንገድ ጥገና ክፍል ማኔጂንግ ዳይሬክተር የሆኑት አቶ ዳንኤል ደመቀ፣ አየር መንገዱ አውሮፕላን ከመጠገን ባለፈ፣ ለአውሮፕላን በረራ መቆጣጠሪያ የሚያገለግሉ ‘RF ኬብሎችን’ በማምረት ለዓለም አቀፉ ቦይንግ ኩባንያ እያቀረበ እንደሚገኝ ገልጸዋል፡፡

ምንም እንኳን በዓለም አቀፍ ደረጃ የጥገና ግብዓቶች እጥረት ቢኖርም፣ አየር መንገዱ ለአፍሪካ እና ለመካከለኛው ምስራቅ ሀገራት በሚሰጠው የጥገና አገልግሎት በሚሊዮን የሚቆጠር ዶላር ገቢ እያስገኘ መሆኑ ተመላቷል።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ አሁን ላይ ከአፍሪካ አየር መንገዶች ጋር ሳይሆን ከዓለም አቀፍ ግዙፍ ተቋማት ጋር የሚፎካከርበት ደረጃ ላይ መድረሱን የዘርፉ ባለሙያዎች መስክረዋል።

በዓለም አቀፍ ደረጃ በተከሰቱት የተለያዩ ችግሮች ምክኒያት የአውሮፕላን ጥገና ግብዓት ችግሮች ቢኖሩም፣ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግን ለአፍሪካ እና ለመካከለኛ ምስራቅ አየር መንገዶች የጥገና አገልግሎት በመስጠት በሚሊዮን ዶላር የሚቆጠር ገቢ እያገኘ መሆኑንም ተነግሯል።

በወርቅነህ አቢዮ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review