AMN- መጋቢት 25/2018 ዓ.ም
በአሁኑ ሰዓት ኢትዮጵያ በነዳጅ ድጎማ ላይ በየወሩ የምታወጣው ከ15 እስከ 20 ቢሊየን ብር በጤና መሰረተ ልማት ላይ ፈሰስ ቢደረግ በአማካኝ 20 ዘመናዊ ሆስፒታሎችን መገንባት የሚችል አቅም ነው።
አሁን ባለው የመካከለኛዉ ምስራቅ ቀውስ ነዳጅን በውድ ዋጋ መግዛት ለመድኃኒት፣ ማዳበሪያና ኢንዱስትሪ ግብዓቶች የሚውለውን የውጭ ምንዛሬ ክምችት ነጥቆ ለነዳጅ መስጠት ነው።
ዓለም አቀፍ የነዳጅ ንግድ ቁልፍ መስመር የሆነው የሆርሙዝ የባሕር ወሽመጥ በኢራን፣ እስራኤል እና አሜሪካ ቀውስ ሳቢያ በመዘጋቱ፣ ኢትዮጵያ ከመካከለኛው ምስራቅ ሀገራት ጋር የነበራት የረጅም ጊዜ የነዳጅ ግብይት ውል ተስተጓጉሏል።
በዚህም፡-
በግዥ ሂደት ላይ የነበረ 180 ሺህ ሜትሪክ ቶን ነዳጅ ወደ ሀገር ውስጥ አልገባም
የነጭ ናፍጣ ዋጋ ከ80 ወደ 230 ዶላር ከፍ ብሏል
ቤንዚን ከ70 ወደ 150 ዶላር አሻቅቧል
የቀን አቅርቦት ከ9.2 ሚሊዮን ሊትር ወደ 4.5 ሚሊዮን ሊትር ዝቅ ብሏል፡፡
ለዚህም መንግስት የአቅርቦት ፍላጎት ለማረጋጋርት በሎም ክፍተቶችን ለመሙላት ፈጣን እርምጃ ወስዷል፡፡
በመጀምሪያ ነዳጅን በቁጠባ እንጠቀም የሚል ሀገራዊ የትብብር ጥሪ በማስተላለፍ ሲሆን በመቀጠልም አቅርቦቱን ለማሳለጥ ከተባራሪ ገበያ ነዳጅ በውድ ዋጋ በመግዛት ለገበያ እያቀረበ ነው፡፡
መንግስት ነዳጅን ከተባራሪ ገበያ ከመደበኛው በሶስት እጥፍ ዋጋ እየገዛ ሲያቀርብ በየወሩ ከ 15 እስከ 20 ቢሊየን ብር ድጎማ እያደረገ ነው፡፡
ይህ ድጎማ በማህበራዊ መሰረተ ልማት ላይ ፈሰስ ቢደረግ በአማካኝ 20 ሆስፒታሎችን የሚገነባ መሆኑን የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር ካሳሁን ጎፌ (ዶ/ር) ትላንት በሰጡት መግለጫ አስታውቀዋል፡፡

ታዲያ ይህን እጅግ ውድ የነሆነው እና በብዙ ጥረት ወደ ሀገር ውስጥ የሚገባውን ነዳጅ በአግባቡ መጠቀም እና መቆጠብ የውጭ ምንዛሬ ከምችትን እንደማዳን ይቆጠራል።
በመሆኑም ይህንን ፈታኝ ወቅት ሁሉም ዜጋ ከመንግስት ጋር በመተባባር፤ ነዳጅን በቁጠባ በመጠቀም ፣ አላስፈላጊ ጉዞዎችን በማስቀረት፣ የሕዝብ ትራንስፖርት በመጠቀም፣ ተሽከርካሪን በሚገባ በመያዝ እና ወደ ኤሌክትሪክ በመቀየር፣ ህገ-ወጥ የነዳጅ ግብይት የሚፈጽሙ አካላት ለህግ በማጋለጥ የኢኮኖሚ ጫናውን በጋራ መወጣት ይገባል፡፡
በትዝታ መንግስቱ