AMN – ሐምሌ 22/2018 ዓ.ም
አብዛኞቹ የግብጽ ፖለቲከኞችና ምሁራን የሃገራቸው ብሄራዊ ጥቅም የሚረጋገጠው የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም በማደናቀፍ ነው ብለው ያምናሉ፡፡
ለዚህም ነው ግብጾች ላለፉት ረጅም ዓመታት ኢትዮጵያ በተፈጥሮ ባገኘችው የውሃ ሃብት እንዳትጠቀም፤ እንዳትለማ፤ ሰላም እንዳታገኝና እንዳትረጋጋ ሲያደናቅፉ የኖሩት፡፡
ግብጾች የኢትዮጵያን ብሄራዊ ጥቅም በማደናቀፍ፤ የራሳቸውን ብሄራዊ ጥቅም ለማረጋገጥ ሲጠቀሙባቸው ከነበሩት ስልቶች ሌላኛው የባህር በር ነው፡፡
ግብጽ በሻዕቢያና በህገ-ወጡ ህወሃት ተላላኪነትና ጉዳይ አስፈጻሚነት ኢትዮጵያ የባህር በር አጥታ ተዘግታ እንድትኖር ማድረጓን ምሁራን ያስረዳሉ፡፡
ኢትዮጵያ እና የባህር በር ለዘመናት አብረው የኖሩ ቢሆኑም ዛሬ ላይ ግን በግብጽ ፤ በሻዕቢያና በህገ-ወጡ የህወሃት ቡድን የረጅም አመታት ታሪካዊ ጥምረት ኢትዮጵያ የባህር ከሌላቸው የዓለም ሃገራት ተርታ ለመሰለፍ ተገድዳለች፡፡
ኢትዮጵያ ለዘመናት አብራው የኖረችውን የባህር በር ያጣችበት መንገድ ፍትሃዊ አለመሆኑና በዚሁ ጉዳይ የኢትዮጵያ መንግስት ከማንም ጋር ያልመከረበት መሆኑ ደግሞ ሃገራችን የባህር በር ያጣችው በአጋጣሚ ሳይሆን የግብጽን ብሔራዊ ጥቅም ለማረጋገጥ መሆኑን ምሁራን ይገልጻሉ፡፡
ኢትዮጵያ በዚሁ በባህር በር እጦት ምክንያት ላለፉት ሶስት አስርት ዓመታት ከ90 በመቶ በላይ የሚሆኑ ከውጭ የሚገቡ እና ወደ ውጭ የሚላኩ ምርቶችንና እቃዎችን የምታስገባው እና የምታስወጣው በጂቡቲ ወደብ በኩል ብቻ እንዲሆን አስገድዷታል፡፡
መረጃዎች እንደሚያመላክቱት ኢትዮጵያ በዓመቱ ለወደብ ኪራይ እስከ ሁለት ቢሊዮን ዶላር ወጪ የምታወጣ ሲሆን ይህም በአጠቃላይ ኢኮኖሚዋና በህዝቡ የእለት ከእለት እንቅስቃሴ ላይ ትልቅ ጫና በመፍጠር ላይ ይገኛል፡፡
ኢትዮጵያ ለንግድና ትራንስፓርት ከምታወጣው ከፍተኛ ወጪ ባሻገር እንደ አንድ ሉዓላዊት ሃገር የባህር በር አጥታ ተዘግታ መኖሯ በቀጣናው ካለው አጠቃላይ የፖለቲካና ንግድ እንቅስቃሴ አንጻር ትልቅ መፍትሔ የሚሻ ጉዳይ መሆኑን ነው ምሁራን እና ፖለቲከኞች የሚናገሩት፡፡
ኢትዮጵያ የባህር በር ያጣችው በግብጽ የረጅም ዘመናት ሴራና ደባ እንዲሁም በሻዕቢያና ህወሃት ጉዳይ አስፈጻሚነት መሆኑ ደግሞ የነዚህ ኃይሎች ዋንኛ ጥምረት ኢትዮጵያን በኢኮኖሚውና በፖለቲካዊ መስክ የማዳከም ተልእኮ መሆኑን በግልጽ የሚያረጋግጥ ነው፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ኢትዮጵያ የባህር በር ያጣችበትን ምክንያት ሲያስረዱ እኛ የቀይ ባሕር ጉዳይ ሕጋዊ፣ ታሪካዊ፣ መልክዓምድራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ጥያቄ ነው ብለን እናምናለን ነው ያሉት፡፡
የሚገባንን መጠየቅ ነውር ብሎ የሚፈርጅ እሳቤ የተዛባ ትርክት ውጤት ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ፍትሃዊ ባልሆነ መንገድ ያጣነው የባህር በር ህጋዊ በመሆነ መንገድ ማግኘት ይገባናል ብለዋል፡፡
የባህር በሩን ለማጣት 30 ዓመት ፈጅቶብናል፤ ነገር ግን የባህር በሩን ለማግኘት ይህንን ያህል ዓመት አይወስድብንም፤ የባህር በር የማግኘት ጉዳይ አይቀሬ ነዉ ሲሉም አክለዋል፡፡
በወንድማገኝ አሰፋ