- ፕላዛዎችን ማስፋፋት አዲስ አበባን የዓለም ከተሞች ከደረሱበት ደረጃ በማድረስ ህዝብን ተጠቃሚ የማድረጉ
አካል እንደሆኑ ተጠቁሟል
አዲስ አበባ ባለፉት ጥቂት ዓመታት ያከናወነቻቸው ተግባራት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየፈካች፣ ስሟንና ያላትን ድርብርብ ሚና የሚመጥን ከተማ እየሆነች እንድትመጣ አድርጓታል፡፡ የከተማዋን ገፅታና መልክ በመቀየር ረገድ የኮሪደር ልማቱ ጉልህ ሚና እየተጫወተ ይገኛል፡፡ ልማቱ ይዟቸው ከመጣ በረከቶች መካከል ህብረተሰቡ በእግሩ እየተንቀሳቀሰ እየተዝናና የሚገበያይባቸው የተለያዩ አገልግሎቶችን አካትተው የያዙ ፕላዛዎች ተጠቃሽ ናቸው፡፡ አራት ኪሎ፣ ሳር ቤት፣ ቴዎድሮስ አደባባይ ፕላዛዎች ከሚገኝባቸው የከተማዋ አካባቢዎች መካከል ናቸው፡፡
ከሁለት ሳምንት በፊትም ከፒያሳ በቸርቸል መንገድ ወደ ቴዎድሮስ አደባባይ ወረድ ብሎ በስተቀኝ በኩል የሚገኘው የድል ፕላዛና የቁርጡሚ የወንዝ ዳርቻ ልማት ግንባታ ተጠናቅቆ ለአገልግሎት ክፍት ሆኗል፡፡ በምርቃ ስነ ስርዓቱ ላይ የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ ወይዘሮ አዳነች አቤቤ እንደተናገሩት፣ የቆሻሻ መጣያ፣ ሰዎች ላስቲክ ወጥረው የሚኖሩበት፣ ገደላማና ለኑሮ የማይመች፣ ጥቅም ላይ ያልዋለ አካባቢ ነበር፡፡ ይህንን ቦታ በመልሶ ማልማት የተንጣለሉ ሱቆች፣ ከመሬት በታች ባለ ሶስት ወለል በአንድ ጊዜ አምስት መቶ ተሽከርካሪዎችን ማቆም የሚያስችሉ ዘመናዊና በቴክኖሎጂ የተደራጀ የመኪና ማቆሚያ፣ አረንጓዴ ስፍራ፣ የስፖርት ሜዳ፣ የህጻናት መጫወቻ፣ አምፊ ቴአትር፣ የስጦታ እቃ መሸጫዎች፣ ሁለት ትላልቅ የቡና መሸጫ ካፍቴሪያዎች እንዲገነቡበት ተደርጓል። የመኪና ማቆሚያው የንግድ ማእከል ከሆኑት ተክለ ሃይማኖትና መርካቶ በቅርብ ርቀት ላይ የሚገኝ ስትራቴጂክ ስፍራ በመሆኑ ሰዎች ወደ እነዚህ ቦታዎች በመሄድ ንግዳቸውን በቀላሉ እንዲያከናውኑ ዕድል ይፈጥርላቸዋል፡፡
አካባቢው በርካታ ቅርሶች የሚገኙበት እንደመሆኑ ለዚህም የሚመጥን አገልግሎት ማቅረብ የሚችሉ እንደዮድ አቢሲኒያ ባርና ሬስቶራንት እንዲሁም የተለያዩ የስጦታ እቃዎችን ማቅረብ የሚችሉ ተቋማት እየሰሩበት ይገኛሉ፡፡ በፕላዛው አገልግሎት መስጠት ከጀመሩት መካከል ዮዲ አቢሲኒያ የባህል ምግብ አዳራሽ አንዱ ነው፡፡ የዮድ አቢሲኒያ መስራችና ባለቤት አቶ ትዛዙ ኮሬ ፕላዛው በተመረቀበት ወቅት እንደተናገሩት፣ የከተማ አስተዳደሩ ከገነባቸው ውብና ማራኪ ህንጻዎች መካከል አንዱን ዮድ አቢሲኒያ የባህል ምግብ አዳራሽ በኪራይ አገልግሎት እንዲሰጥበት ባስተላለፈው ውሳኔ መሰረት በአጭር ጊዜም አስፈላጊ እቃዎችን በማሟላት በተደራጀ መንገድ ወደ ስራ መግባታቸውንና ለዚህም ምስጋናቸውን አቅርበዋል፡፡ ድርጅቱ የኢትዮጵያን ቱባ ባህልና የቱሪዝም ሀብቶች ለዓለም በማስተዋወቅ፣ መልካም ገፅታ በመገንባት፣ ሰፊ የሥራ ዕድል በመፍጠር፣ ለመንግስት ከፍተኛ ገቢ በማስገኘት ባበረከተው አስተዋፅኦ “የኢትዮጵያ የባህልና ቱሪዝም አምባሳደር” የሚል እውቅና ከመንግስት ተሰጥቶታል። ድርጅቱ ስራውን በሰፊው ማከናወን እንዲችል በቀድሞ ካዛንቺስ ቶታል አካባቢ የግንባታ ቦታ እንደተሰጠው ያነሱት አቶ ትዛዙ፣ መንግስት ለአልሚዎች የሚጨነቅ፣ ሱቅ ሲፈርስ ሱቅ የሚተካ፣ የንግድ ድርጅት ገንብቶ የሚሰጥ መሆኑን ከእነሱ በላይ ማስረጃ እንደሌለ አንስተዋል፡፡ ይህም ለስራ ፈጣሪዎች ተነሳሽነት የሚፈጥር እንደሆነና ለዚህም ለአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ ወይዘሮ አዳነች አቤቤና ለከተማው አመራሮች ምስጋና አቅርበዋል፡፡
የድል ፕላዛን በማሳያነት አነሳን እንጂ ከአንድ ዓመት በፊት ተገንብቶ ወደ ስራ የገባው የአራት ኪሎ ፕላዛ ከተማዋ ልዩ ገፅታ እና ዘመናዊነትን እንድትላበስ ከማስቻሉም ባሻገር የተነቃቃ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ እንዲኖር ከፍተኛ ሚና እየተጫወተ ይገኛል፡፡ በፕላዛው የምድር ውስጥ መሸጋገሪያ ዋሻ እግረኞች ደህንነታቸው ተጠብቆ ከአንዱ የመንገድ አካል ወደ ሌላው ሲያቋርጡ፤ በተለያዩ የንግድ ሱቆችም ሲገበያዩና ሲዝናኑ ይታያል፤ በሱቆቹ ከሚሸጡ ምርቶችና አገልግሎቶች መካከል የሞባይልና ስልክ መለዋወጫዎች፣ የጽሕፈት መሳሪያዎች፣ መጽሀፍ መሸጫዎች፣ መነፅር ቤቶች፣ የኤሌክትሮኒክስ ውጤቶች፣ አልባሳትና ካፌዎች ይገኙበታል፡፡ ሱቆቹ ከተለመደው የስራ ሰዓት በዘለለ ከጠዋቱ 12፡30 እስከ ምሽቱ 3፡00 ድረስ ክፍት ሆነው አገልግሎት ይሰጥባቸዋል፡፡
የፈረንሳይ አካባቢ ነዋሪው ወጣት ሻምበል ግርማ የባንክ ባለሙያ ሲሆን የስራ ቦታውም ፕላዛው ባለበት አካባቢ እንደመሆኑ አራት ኪሎን በደንብ እንደሚያውቀው ይናገራል፡፡ አራት ኪሎ ከዚህ በፊት የነበረው ገፅታ ደስ የማይል ነበር፡፡ በመንገዶች ይካሄዱ የነበሩ የጎዳና ላይ ንግዶች፣ በመንገድ ዳር የቆሙ የማስታወቂያ ሰሌዳዎች ለእይታ የማይስቡና የሰዎችን እንቅስቃሴ የሚገድቡ ነበሩ፡፡ በአሁኑ ወቅት እነዚህ ችግሮች ተቀርፈዋል፤ የአካባቢው ገፅታ ተቀይሯል፤ ዘመናዊነትን ተላብሷል። በፕላዛው ምድር ውስጥ ባሉት ሱቆች የተለያዩ አገልግሎቶች ይገኛሉ፡፡ እንደዚህ ዓይነት ንግድና መዝናኛን ያማከሉ ዘመናዊ ማዕከላት በየአካባቢው መስፋፋት እንዳለባቸው ይገልጻል፡፡
በአራት ኪሎ የመኪና ማቆሚያና የገበያ ማዕከል ውስጥ ተሽከርካሪያቸውን አቁመው ሲወጡ ያገኘናቸው አቶ ቢኒያም ተስፋሁን፣ “ፕላዛው የአካባቢውን ውበትና ገፅታ ከመቀየር ባሻገር ዘርፈ ብዙ አገልግሎቶች በአንድ አካባቢ የሚገኝበት በመሆኑ ለነዋሪው ከፍተኛ ጥቅም ያስገኛል፡፡ ለምሳሌ፡- ከዚህ ቀደም በቂና ደህንነቱ የተጠበቀ የመኪና ማቆሚያ ባለመኖሩ መንገድና ደህንነቱ ያልተጠበቀ ቦታ ተሽከርካሪ አቁሜ ስፖኪዮና የተለያዩ የመኪና አካላት መሰረቅ አጋጥሞኝ ነበር፡፡ አሁን ደህንነቱ በተጠበቀ መልኩ አገልግሎቱን እንድናገኝ አስችሎናል” ሲሉ ፋይዳውን አብራርተዋል፡፡
ሌላው በጦር ሀይሎች አካባቢ ነዋሪ የሆኑት አቶ ማናዬ እሱባለው ለስራ ወደ አራት ኪሎ በመጡበት አጋጣሚ ፕላዛው ውስጥ ካሉት ሱቆች እንደ አትክልትና ስኳር ያሉ የፍጆታ ምርቶችን ሸምተው ሲወጡ ነበር ያገኘናቸው፡፡ “እንደዚህ ዓይነት ገበያዎች መበራከታቸው ይበል የሚያሰኝ ነው፡፡ በተመጣጣኝ ዋጋ የፈለግነውን ምርትና አገልግሎት መሸመት እንድንችል እድል ፈጥሮልናል፡፡ ሱቆቹ የሚገኙበት ቦታ ማዕከላዊ በመሆኑ፣ የፈለግነውን እንድንሸምትና በዚህም ጊዜና ጉልበት እንድንቆጥብ አስችሎናል፡፡ አካባቢው ፅዱ እና ሰፊ በመሆኑ እንደ ልብ ለመንቀሳቀስ ያስችላል፡፡ በተጨማሪም ንጹህና ጥራቱን የጠበቀ ምርትም እያገኘን ነው፡፡” ሲሉ እያስገኙት ስላለው ጥቅም ገልጸዋል፡፡
ፕላዛዎቹ ለሸማቹ ብቻ ሳይሆን ለበርካቶች በተለያየ የንግድ ዘርፍ የስራ ዕድል ፈጥረዋል፡፡ ወጣት ሜላት ንገሴ በአራት ኪሎ ፕላዛ የምድር ውስጥ መተላለፊያ ባላት ሱቅ ጫማና ቦርሳዎችን ትሸጣለች፡፡ ፕላዛው ከዚህ ቀደም ያልነበረ፣ አዲስ አበባን ልዩ ውበትና ዘመናዊነትን ያላበሰ እንደሆነ የምትገልፀው ወጣት ሜላት፣ ሰዎች በአካባቢው ሲሸጋገሩ እግረመንገዳቸውን በቀላሉ መገበያየት እንዲችሉ ጥሩ እድል መፍጠሩንም ትናገራለች፡፡
ፕላዛዎቹ እንደሷ ላሉ ወጣቶች የስራ ዕድል የሚፈጥሩ መሆናቸውን የምትናገረው ወጣት ሜላት፣ በአካባቢው አስተማማኝ የ24 ሰዓት ጥበቃ ስላለ ያለምንም የደህንነት ስጋት ንግዳቸውን እንዲያቀላጥፉ እድል ፈጥሮላቸዋል። ከጠዋት አንስቶ እስከ ምሽት 3፡00 ድረስ እንደሚሰሩና ከጊዜ ወደ ጊዜ ሰዎች መንገድ ብቻ ሳይሆን ሱቆችም እንዳሉ በመረዳት እየመጡ እየተገበያዩ እንደሆነ ገልጻለች፡፡
ሌላኛው የስራ ዕድል የተፈጠረላቸው በፎቶ ኮፒ (የጽህፈት) አገልግሎት እየሰሩ የሚገኙት አቶ ተገኝ አለሙ ናቸው፡፡ አቶ ተገኝ በአንድ የመንግስት መስሪያ ቤት ይሰራሉ፡፡ ባለቤታቸው ደግሞ ከዚህ ቀደም ስራ ስላልነበራቸው ቤት ውስጥ ነበር የሚውሉት፡፡ የፕላዛውን መከፈት ተከትሎ በጨረታ በተመጣጣኝ ኪራይ ሱቅ ማግኘት እንደቻሉና በጀመሩት ስራም ተጠቃሚ እንደሆኑ ተናግረዋል፡፡
አካባቢው ከፍተኛ የትምህርት ተቋም የሚገኝበት በመሆኑ ለተማሪዎች ከጽህፈትና ፎቶ ኮፒ ጋር በተያያዘ የተለያዩ አገልግሎቶችን እየሰጡ እንደሚገኙም አክለዋል፡፡
የፕላዛዎች ኢኮኖሚያዊ አበርክቶ
በተባበሩት መንግስታት በአስተዳደር፣ ድህነት እና ዘላቂ ጉዳዮች ላይ ከፍተኛ የፖለሲ አማካሪ፣ በአፍሪካ ሰብዓዊ ኔትዎርክና የተለያዩ የጥናትና ምርምር ተቋማት ቦርድ ሰብሳቢና አባል በመሆን የሰሩት ቆስጠንጢኖስ በርኸተስፋ (ዶ/ር) ለዝግጅት ክፍላችን እንደገለፁት፣ በከተማዋ ተገንብተው ለአገልግሎት ክፍት እየሆኑ የሚገኙት ፕላዛዎች ዘርፈ ብዙ ፋይዳ አላቸው፡፡ ፕላዛዎች ሰዎች የሚገናኙባቸው፣ የሚገበያዩባቸው፣ የሚዝናኑባቸው ሰፋ ያሉና ክፍት ቦታዎች ያሉባቸው ናቸው፡፡ በአሜሪካ ታዋቂውን የኒውዮርክ ሴንተራል ፓርክን መጥቀስ ይቻላል፡፡ በአውሮፓና በተለያዩ አገራት ባሉ ከተሞችም የተለመዱ ናቸው፡፡
በአዲስ አበባ ከዚህ ቀደም ሰዎች በመንገድ ዳር፣ በቆርቆሮ በታጠሩ ቤቶች ውስጥ ይሰሩ ነበር፡፡ ፕላዛዎች መገንባታቸው በተደራጀ መልኩ በአንድ አካባቢ የተለያዩ ምርትና አገልግሎቶችን የሚያገኙበት ሁኔታ መፈጠሩ ኑሮን የሚያቀል፤ የከተማዋን ገፅታ የሚቀይርና ድምቀትን የሚያላብስ ነው፡፡ ተጠቃሚው ንጹህ፣ አድራሻው በታወቀ ቦታ የሚገበያይበት ሁኔታ መፈጠሩ ዋጋው በኢኮኖሚ ብቻ የሚመነዘር አይደለም። በሱቆች የሚቀመጡ ቁሳቁሶች፣ በካፌና ሬስቶራንቱ የሚስተናገዱ ሰዎች ደረጃውን በጠበቀ መልኩ አገልግሎት ማግኘታቸው ወይም መስጠታቸው በንጽህና ጉድለት የሚመጡ በሽታዎችን በመከላከል ረገድ ትልቅ ፋይዳ ይኖረዋል፡፡
የምጣኔ ሀብት ምሁሩ ቆስጠንጢኖስ (ዶ/ር) እንደሚገልጹት፣ የድል ፕላዛ ተመርቆ መከፈቱ የከተማዋን ኢኮኖሚ በማነቃቃት ከፍተኛ ጥቅም ያስገኛል፡፡ ለምሳሌ፡- ከዚህ ቀደም በቂ የተደራጁ የመኪና ማቆሚያ ስፍራዎች ባለመኖራቸው፣ በከተማዋ በተለያዩ አካባቢዎች የሚገኙ መንገዶች ቀለም እየተቀቡ የመኪና ማቆሚያ ሆነው ነበር። አሁን ከፕላዛዎች ጋር የተደራጁ የመኪና ማቆሚያዎች በመሰራታቸው መንገድ ላይ አይቆሙም፤ በዚህም ምክንያት የትራፊክ እንቅስቃሴው የተሳለጠ ሆኗል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ የትራፊክ አደጋን መቀነስ ተችሏል፡፡ በፕላዛዎች ለመገበያየት፣ ለመዝናናት፣ ለመገናኘት የሚመጡ ሰዎችም መኪናቸውን ደህንነቱ በተጠበቀ ቦታ በማቆም የሚፈልጉትን አገልግሎት የሚያገኙበት ሁኔታ ተፈጥሯል፡፡
ፕላዛዎች የህዝብ የጋራ መገልገያ የሆኑ የንግድ ሱቆች፣ የመኪና ማቆሚያዎች፣ የተለያዩ መዝናኛዎችን የሚያካትቱ የከተማ መታደስ ምልክቶች ናቸው፡፡ በዚህ ረገድ ፕላዛዎችን ማስፋፋት አዲስ አበባን የዓለም ከተሞች ከደረሱበት ደረጃ በማድረስ ህዝብን ተጠቃሚ የማድረጉ አካል እንደሆነ የምጣኔ ሀብት ምሁሩ ቆስጠንጢኖስ (ዶ/ር) ተናግረዋል፡፡
የአዲስ አበባ ከንቲባ ወይዘሮ አዳነች አቤቤ የድል ፕላዛና የቁርጡሚ የወንዝ ዳርቻ ልማት መጠናቀቅን አስመልክቶ በይፋዊ ማህበራዊ ትስስር ገጻቸው እንዳሰፈሩት፣ የአዲስ አበባ የኮሪደር ልማትና መልሶ ማልማት ስራ አነስተኛ ቢዝነሶችን የሚያዳክም ሳይሆን ይበልጥ ዘመናዊ፣ ለስራ እና ለሸማቹ ሳቢ በሆነ መንገድ እንዲሰሩ እድል ፈጥሯል፡፡ የድል ፕላዛ እና የቁርጡሚ ወንዝ ዳርቻ ቀደም ሲል ከቦሌ አትላስ እስከ ብራስ መንገድ በኮሪደር ልማቱ ምክንያት ተነስተው የነበሩ የንግድ ተቋማት በፕላዛው ውስጥ በተገነቡ ሱቆች ስራቸውን እንዲጀምሩ መደረጉን ለማሳያነት አንስተዋል፡፡
በጥቅሉ ፕላዛዎችና አደባባዮች በተለያየ መልኩ ለከተሞች የኢኮኖሚ እድገት ሞተር ሆነው ማገልገል ይችላሉ፡፡ በፕላዛው አካባቢ ያሉ የንግድ እንቅስቃሴዎችን በማነቃቃት፣ ኢንቨስትመንትንና ቱሪዝምን በማበረታታት፣ የስራ ዕድል በመፍጠር ከፍተኛ ጠቀሜታ እንዳላቸው በዘርፉ የተጻፉ መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡
በስንታየሁ ምትኩ