AMN-ግንቦት 6/2018 ዓ.ም
ዓለም አቀፍ የሙዚየም ቀን ግንቦት 10 ቀን 2018 ዓ.ም በዓድዋ ድል መታሰቢያ በልዩ ሁኔታ እንደሚከበር ተገለጸ።
ዓለም አቀፍ የሙዚየም ቀንን የዓድዋ ድል መታሰቢያ እና የኢትዮጵያ ቅርስ ባለሥልጣን በጋራ በመሆን የሚያዘጋጁት ሲሆን ፣ “ሙዚየሞች የተከፋፈለውን ዓለም ያስተሳስራሉ” በሚል መሪ ቃል ይከበራል። የበዓሉን አከባበር አስመልክቶ ተቋማቱ በጋራ ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተዋል።
የዓድዋ ድል መታሰቢያ ዋና ዳይሬክተር ዮሴፍ ቤኮ (ዶ/ር)፣ መታሰቢያው ለዘንድሮው ዓለም አቀፍ የሙዚየም ቀን ክብረ በዓል አስተናጋጅ በመሆኑ የተሰማቸውን ደስታ ገልጸዋል።

ዳይሬክተሩ የዓድዋ ድል መታሰቢያ የታሪክ ማዕከል ብቻ ሳይሆን የአፍሪካውያን የአንድነት እና የነፃነት ምልክት መሆኑን ጠቁመው፤ ዕለቱ ይህንን ታላቅ እሴት ለዓለም ለማሳወቅ መልካም አጋጣሚ እንደሚፈጥር ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ ቅርስ ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር ረዳት ፕሮፌሰር አበባው አያሌው ፣ ሙዚየሞች ካለፈው ታሪክ የምንማርባቸው ብቻ ሳይሆኑ ለወደፊት ግባችን እንደ ድልድይ የሚያገለግሉ መሆናቸውን አጽንኦት ሰጥተዋል።
ረዳት ፕሮፌሰሩ አክለውም “ዓድዋ የኢትዮጵያውያን ብቻ ሳይሆን የመላው ጥቁር ሕዝብና የተገፉ ሕዝቦች ሁሉ የድል ምልክት በመሆኑ፣ ይህ በዓል እዚህ መከበሩ ድሉ ያለውን ዓለም አቀፋዊ ትስስር ይበልጥ ያጎላዋል” ሲሉ ገልጸዋል።

ሙዚየሞች የሀገርን ሉዓላዊነትና ማንነት ጠብቀው የሚያቆዩ ተቋማት በመሆናቸው፣ ማህበረሰቡ ለቅርሶችና ለሙዚየሞች የሚሰጠው ትኩረት ሊያድግ እንደሚገባም ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል።
ዘንድሮ የሚከበረው የሙዚየም ቀን፣ የኢትዮጵያን ቅርሶችና ሙዚየሞች ለቱሪዝም እና ለባህል ልውውጥ ያለውን ፋይዳ ለማሳደግ ታሳቢ ያደረገ መሆኑንም ገልጸዋል።
በዕለቱ የተለያዩ ጥናታዊ ፅሁፎች፤ የፓናል ውይይቶችና የሙዚየም ጉብኝቶችን ያካተቱ መርሃ-ግብሮች እንደሚከናወኑ መገለጹን ከዓድዋ ድል መታሰቢያ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።