AMN- መጋቢት 26/2018 ዓ.ም
ኢትዮጵያ የመድኃኒት ፍላጎቷን በሀገር ውስጥ ምርት ለመሸፈን በምታደርገው ጥረት ከፍተኛ ስኬት እያስመዘገበች መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገልጸዋል።
በኢትዮጵያ እና በአፍሪካ የሳይንስ ሥነ-ምሕዳር ውስጥ አዲስ ምዕራፍ የሚከፍት ዘመናዊ የምርምር ማዕከል በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ተመርቆ ለአገልግሎት ክፍት ሆኗል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በምረቃ መርሐ ግብሩ እንደገለጹት፣ በኮሮና ወረርሽኝ ወቅት የታየው የዓለም አቀፍ መድኃኒት እጥረትና አድልዎ እንደ ትልቅ ትምህርት ተወስዶ፣ ሀገሪቱ በመሰረታዊ ፍላጎቶች (ምግብ፣ ልብስ እና መድኃኒት) ሉዓላዊነቷን ለማረጋገጥ ስትሰራ ቆይታለች ብለዋል።
በኮቪድ ወረርሽኝ ወቅት የሀገር ውስጥ የመድኃኒት ምርት አቅም 8 በመቶ ብቻ እንደነበር የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ባለፉት ጥቂት ዓመታት በተደረገ ሰፊ ኢንቨስትመንትና የላብ ሥራ በአሁኑ ወቅት ወደ 44 በመቶ ማደጉን ተናግረዋል።

በሚቀጥሉት ሁለት ሳምንታት የሚመረቁ አዳዲስ ፋብሪካዎችን ጨምሮ፣ በዘንድሮው ዓመት ምርቱ ከ50 እስከ 55 በመቶ እንደሚደርስ ይጠበቃል ብለዋል፡፡
መንግስት በሚቀጥሉት አምስት ዓመታት ውስጥ ኢትዮጵያ ለራሷ የሚያስፈልጋትን መድኃኒትና ክትባት ሙሉ በሙሉ በሀገር ውስጥ የማምረት ግብ አስቀምጦ እየሰራ መሆኑንም ነው ያመላከቱት።
ይህም “ምግብ፣ ልብስና መድኃኒት ለሀገር ሉዓላዊነት ወሳኝ ናቸው” በሚል እሳቤ የሚመራ እንደሆነ አስገንዝበዋል።
በታምራት ቢሻው