AMN- መጋቢት 28/2018 ዓ.ም
ከተሜነትን ማስፋፋትና ከተሞችን በዘመናዊ መልክ መልሶ ማልማት የኢኮኖሚ እድገትን ለማፋጠን፣ የሥራ ዕድል ለመፍጠርና የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንትን ለመሳብ ወሳኝ ሚና እንዳለው የኢኮኖሚ ምሁር ገለጹ።
በዋቸሞ ዩኒቨርሲቲ የኢኮኖሚክስ ትምህርት ክፍል መምህር የሆኑት በረከት አድማሱ ከኤ ኤም ኤን ዲጂታል ጋር ባደረጉት ቆይታ፤ በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ በተለይም በአዲስ አበባ እየተከናወነ ያለው የኮሪደር ልማት በኢኮኖሚው ላይ የሚያስገኘውን ዘርፈ-ብዙ ፋይዳ አብራርተዋል።
እንደ መምህር በረከት ገለጻ ፤ ከተማን ማዘመን የኢኮኖሚ እድገት ቀጥተኛ መገለጫ ነው፡፡ ከተሞች ሲዘምኑ የንግድ እንቅስቃሴዎች ይነቃቃሉ፣ የኢንቨስትመንት ፍሰትም ይጨምራል።
በተለይም አሁን ባለው ተጨባጭ ሁኔታ የኮሪደር ልማቱ ለበርካታ ዜጎች አዳዲስ የሥራ ዕድሎችን እየፈጠረ ይገኛል።

በፊት ለመተላለፊያ እንኳን የማይበቁ መንገዶች በልማቱ ምክንያት በመስፋፋታቸው፣ ወጣቶች በፎቶ ኤግዚቢሽንና በተለያዩ የንግድ ሥራዎች ላይ እየተሳተፉ ነው ያሉት ኢኮኖሚክስ መምህሩ ይህም በቀጥታ የነዋሪዎችን ገቢ ለማሳደግ እንደሚረዳ ጠቁመዋል።
የኮሪደር ልማቱ ለንግድ እንቅስቃሴ እንደ ‘ደም ዝውውር’ ነው ሲሉ ልማቱ የትራንስፖርት ወጪንና ጊዜን በመቀነስ ረገድ ያለውን ጠቀሜታ አብራርተዋል፡፡
የትራፊክ መጨናነቅ ሲቀንስ ሸቀጦች በፍጥነትና በዝቅተኛ ወጪ ለተጠቃሚው ይደርሳሉ፣ ይሄ ደግሞ የምርት ወጪን ቀንሶ ትርፋማነትን ይጨምራል ብለዋል።
በተጨማሪም ሰፊ የመንገድ አማራጮች መፈጠራቸው ሸማቾች በምቾት እንዲገበያዩና የንግድ ፍላጎት እንዲጨምር ማድረጉን ጠቅሰዋል።
አዲስ አበባ የበርካታ ዓለም አቀፍ ተቋማት መቀመጫ እንደመሆኗ፣ ከተማዋን ማዘመን የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንትን ለመሳብና የቱሪዝም ገቢን ለማሳደግ እንደሚረዳ ነው በዋቸሞ ዩኒቨርስቲ የኢኮኖሚክስ መምህሩ በረከት አድማሱ የገለጹት፡፡ ይህም የሀገሪቱን የውጭ ምንዛሬ ክምችት ለማሳደግ የጎላ አስተዋጽኦ ይኖረዋል።
የከተማ ማዘመን ስራው ኢኮኖሚው የተለያዩ ዓለም አቀፋዊ ጫናዎችን የመቋቋም አቅሙን እንደሚያሳድገው በመጠቆም ፣ ልማቱ ተጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባ አስገንዝበዋል።
በታደሰ ሽፈራው