በደቡብ ሱዳን የሚገኙ የቤተክርስቲያን መሪዎች እና ፖለቲከኞች የትንሳኤን በዓል ምክንያት በማድረግ ዘላቂ ሰላም እንዲሰፍን ጠየቁ

You are currently viewing በደቡብ ሱዳን የሚገኙ የቤተክርስቲያን መሪዎች እና ፖለቲከኞች የትንሳኤን በዓል ምክንያት በማድረግ ዘላቂ ሰላም እንዲሰፍን ጠየቁ

AMN – መጋቢት 29/2018 ዓ.ም

በደቡብ ሱዳን የሚገኙ የቤተክርስቲያን መሪዎች እና ፖለቲከኞች የትንሳኤን በዓል ምክንያት በማድረግ ባስተላለፉት መልእክት በሀገሪቱ የሚታየዉ ግድያ እና ግጭት እንዲቆም እና ዘላቂ ሰላም እንዲሰፍን ጥሪ አቅርበዋል።

የጁባ ቅድስት ቴሬዛ ካቴድራል ረዳት ሊቀ ጳጳስ ሳንቶ ሎኩ ፒዮ ባስተላለፉት መልእክት “ክርስቲያኖች ጥላቻን ፤ አመጽን እና ግድያን መለማመድ የለባቸዉም፤ ንጹሃንን አትግደሉ፤ የሰላም ሰው ሁኑ፤ የትንሳኤ ትርጉሙም ይኸው ነው ሲሉ መልእክት አስተላልፈዋል፡፡

ረዳት ጳጳሱ የደቡብ ሱዳን መሪዎች ሰላም እንዲሰፈን በብርቱ ሊተጉ እንደሚገባ መልእክታቸዉን አስተላልፈዋል፡፡ ትክክለኛውን ነገር እናድርግ፣ ያኔ ሰላም ይነግሳል ብለዋል፡፡

ባለፈው ሳምንት ከጁባ በደቡብ ምዕራብ በሚገኘው ጀበል-ኢራቅ የማዕድን ስፍራ 74 የማዕድን ሠራተኞች በታጠቁ ኃይሎች መገደላቸዉ ይታወቃል፡፡

የደቡብ ሱዳን ፕሬዝዳንት ሳልቫ ኪር የትንሳኤን በዓል ምክንያት በማድረግ በፕሬዝዳንቱ የፕሬስ ፀሐፊ አማካኝነት በቅድስት ቴሬዛ ካቴድራል ባስተላፉት መልዕክት “ትንሳኤ በጨለማው ወቅት እንኳን ተስፋ መቁረጥ እንደሌለብን የምናስታውስበት ጊዜ ነው” ብለዋል።

“እርስ በርሳችን ይቅር እንባባል፣ እንረዳዳ፣ እጅ ለእጅም ተያይዘን የህዝባችንን ጥንካሬ እና ክብር የሚያንጸባርቅ ሀገር እንገንባ” ሲሉ ጥሪ አቅርበዋል።

ሌሎች የሃይማኖት መሪዎችም በደቡብ ሱዳን ያለውን ዓመፅ ለማስቆም እና በመላ ሀገሪቱ ሰብአዊ ክብርን ለመመለስ አስቸኳይ እርምጃ ያስፈልገናል ሲሉ አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡

የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ደቡብ ሱዳን ዳግም ወደ ከፍተኛ የእርስ በርስ ጦርነት ልታመራ እንደምትችል በተደጋጋሚ ማስጠንቀቂያ መስጠቱ ይታወሳል፡፡

ደቡብ ሱዳን እ.ኤ.አ. በ2011 ከሱዳን ነፃነቷን ያገኘች የአለማችን ትንሿ ሀገር ናት።

በወንድማገኝ አሰፋ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review