የምግብ ዋስትናን ማረጋገጥ ለአምራች ኃይል ግንባታ የጀርባ አጥንት ነው – ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ

You are currently viewing የምግብ ዋስትናን ማረጋገጥ ለአምራች ኃይል ግንባታ የጀርባ አጥንት ነው – ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ

AMN – መጋቢት 29/2018 ዓ.ም

የምግብ እና ሥርዓተ ምግብ ዋስትናን ማረጋገጥ፣ ለሀገራችን ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ዕድገት መሳካት ቁልፍ ሚና ላለው አምራችና ተመራማሪ ኃይል ግንባታ ያለው አስተዋጽኦ ከፍተኛ መሆኑን ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ተመስገን ጥሩነህ ገለጹ።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማኅበራዊ ትስስር ገጻቸው ባስተላለፉት መልእክት፤ በምግብ ሥርዓት ትራንስፎርሜሽን፣ በሥርዓተ ምግብና ሰቆጣ ቃል ኪዳን፣ በጤና መድህን፣ በ”ጽዱ ኢትዮጵያ” ንቅናቄና በጤና ኤክስቴንሽን ፕሮግራም ማሻሻያ የ2018 ዓ.ም የስድስት ወራት ዕቅድ አፈጻጸም ላይ በበይነ መረብ ሰፊ ውይይት ማካሄዳቸውን አስታውቀዋል።

በፌዴራል ደረጃ የተከለሰው የምግብ ሥርዓት ትራንስፎርሜሽን ፍኖተ ካርታ መጽደቁ የተገለጸ ሲሆን፣ በፍኖተ ካርታው የታቀዱ ቁልፍ ተግባራት በየዘርፍ መሥሪያ ቤቶቹና በክልል ቢሮዎች ዕቅድ ውስጥ ተካተው ወደ ትግበራ እንዲገቡ አቅጣጫ ተቀምጧል።

በተጨማሪም የፌዴራል የምግብ ሥርዓትና ሥርዓተ ምግብ ምክር ቤት ማቋቋሚያ ረቂቅ አዋጅ ላይ በመወያየት፣ የባለድርሻ አካላት ግብዓት ታክሎበት ወደ ቀጣይ ምዕራፍ እንዲሸጋገር ተወስኗል።

የሰቆጣ ቃል ኪዳን ትግበራ ወሳኝ ምዕራፍ ላይ መድረሱን የጠቆሙት አቶ ተመስገን፤ በ15 ዓመቱ ፍኖተ ካርታ መሠረት የመጨረሻው የአምስት ዓመት የማስፋፊያ ምዕራፍ (ከ2019 – 2023 ዓ.ም) የትግበራ ዕቅድ መጽደቁን ገልፀዋል።

በዚህም መቀንጨርንና ሌሎች የሥርዓተ ምግብ ችግሮችን በፍጥነት ለመቀነስ የተገኙ ተሞክሮዎችን በመቀመር ማኅበረሰቡን በባለቤትነት ማሳተፍ እንደሚገባ አሳስበዋል።

በክልል ደረጃ ጠንካራ አስፈጻሚ አካላትን በማደራጀትና በበጀት ዓመቱ የፌዴራል ቋት መመስረት በሚቻልበት ሁኔታ ላይ መግባባት ተፈጥሯል።

ጤና መድህን ያለው ለሌለውን የሚደጋገፍበት ወሳኝ ፕሮግራም ነው ያሉት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ የመክፈል አቅምን መሠረት ያደረገ የመዋጮ ሥርዓትን በማጠናከር ሁሉንም የማኅበረሰብ ክፍል ማሳተፍ እንደሚገባ ገልጸዋል።

የጽዱ ኢትዮጵያ ማስፋፊያ አድቮኬሲና የጤና ኤክስቴንሽን ፕሮግራም ማሻሻያ የ5 ዓመታት ፍኖተ ካርታ ትግበራ በንቅናቄ ሊመራ እንደሚገባ አቅጣጫ ተቀምጧል።

ለዚህም በፌዴራልና በክልል ደረጃ ለፕሮግራሙ ልዩ ትኩረት በመስጠት በቂ በጀት እንዲመደብና ከተለያዩ ምንጮች የሀብት ማሰባሰብ ተግባራት ተጠናክረው እንዲቀጥሉ መወሰኑን ምክትል ጠቅላይ ሚኒስር ተመስገን በማህበራዊ የትስስር ገፃቸው ባጋሩት መልእክት ገልፀዋል።

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review