AMN – መጋቢት 30/2018 ዓ.ም
መድረኩ በዋናነት በሰላም፣ የሞራል እሴቶች ግንባታ እና በህግ የበላይነት ዙሪያ የህዝብ ተሳትፎን ለማጎልበት ያለመ መሆኑን የአዲስ አበባ ከተማ ሰላምና ፀጥታ አስተዳደር ቢሮ ሀላፊ ወይዘሮ ሊዲያ ግርማ ተናግረዋል፡፡
የ”አውደ ሰላም” የውይይት ፕሮግራም ነዋሪዎች ከአመራሮቻቸው ጋር በቀጥታ የሚመክሩበትና የሰላም ግንባታ ባለቤትነታቸውን የሚያረጋግጡበት መድረክ መሆኑንም የቢሮ ሀላፊዋ ገልጸዋል፡፡
የቢሮ ሀላፊዋ አክለውም አውደ ሰላም የፖሊሲ አውጭዎችና የምሁራን እይታዎች በሰላምና በግጭት ዙሪያ የሚሰነዘሩበት ፕሮግራም መሆኑንም አንስተዋል፡፡

የአዲስ ሚዲያ ኔትዎርክ ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ ካሳሁን ጎንፋ በበኩላቸው የአውደ ሰላም ፕሮግራም በንግግርና በሃሳብ የበላይነት የሚያምን ትውልድ ለመፍጠር በሚደረገው ጥረት አዲስ ሚዲያ ኔትዎርክም የራሱን አስተዋጽኦ ለማበርከት የተጀመረ ፕሮግራም መሆኑን ገልጸዋል፡፡
ሀገራችን በአሁኑ ጊዜ የሚያስፈልጓት እንደነዚህ አይነት መድረኮች መሆናቸውንም አቶ ካሳሁን ገልጸዋል፡፡
አዲስ ሚዲያ ኔትዎርክ በልማት፣ በፖለቲካ፣ በኢኮኖሚ እና በተለያዩ ማህበራዊ ዘርፎች ሲሰራ መቆየቱን ያሰታወሱት ዋና ስራ አስፈፃሚው፣ አሁን ደግሞ የሁሉም መሰረት በሆነው በሰላም ላይ ትኩረት አድርገን ለመስራት ባለን ቁርጠኝነት የአውደ ሰላምን ፕሮግራም አስጀምረናል ብለዋል፡፡

ይህ ፕሮግራም አዲስ ሚዲያ ኔትዎርከ ለማህበረሰቡ ያለውን ተቆርቋሪነትና የሀገር ግንባታ ሚናውን በላቀ ትጋት ለመወጣት የያዘው አዲስ ስትራቴጂ አካል መሆኑም ተመላክቷል
በአስማረ መኮንን