የአረንጓዴ ዐሻራ ንቅናቄ ለኢትዮጵያ የካርቦን ልቀትን በመቀነስ ከሚከናወን ስነ-ምህዳራዊ ግዴታ በላይ ነው !

AMN ሐምሌ 27/2018 ዓ.ም

በኢትዮጵያ ምድር ላይ እየተከናወነ ያለው “የአረንጓዴ ዐሻራ” ንቅናቄ ቀደሞ እንደሚታሰበው በቀላሉ ዛፍ የመትከል አካባቢያዊ ዘመቻ ብቻ ሳይሆን፣ የሃገርን ህልውና በስነ-ምህዳራዊ መሰረት ላይ እንደገና የመገንባትና የትውልድን እጣፈንታ የማደስ ታላቅ ስትራቴጂካዊ ሽግግር ነው።

ይህ ጥረት የተሸረሸረውን የመሬት አካል መልሶ ከመጠገን አልፎ፣ በአየር ንብረት መዛባትና በተፈጥሮ ሃብት መናመን ምክንያት ሊከሰት የሚችለውን ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጉዳት ቀድሞ የማክሸፍ የረጅም ጊዜ ህልውና ዋስትናችን ነው።

ዛፎች ወደ መሬት በሚሰዱት ስር አማካኝነት አፈርን፣ ውሃንና አየርን እንደሚያስተስሩ ሁሉ፣ ይህ ንቅናቄም የሰውን ልጅ ከተፈጥሮ እና ከራሱ መኖሪያ ጋር የሚያስታርቅ፣ ተፈጥሮን ከብዝበዛ ወደ እንክብካቤ ማዕከልነት ያሸጋገረ አዲስ ሀገራዊና አህጉራዊ አስተሳሰብ ነው።

የአረንጓዴ ዐሻራ መርሃ-ግብር የኢትዮጵያን አህጉራዊና አለምአቀፋዊ የታሪክ ድርሻ በአዲስ እይታ የሚያስቀምጥ የመልካም ዲፕሎማሲና የጋራ እድገት ማኒፌስቶ ነው። ይህ ሥራ በድንበር ያልተወሰኑ ወንዞችንና የአየር ንብረት ተፅዕኖዎችን ታሳቢ ያደረገ በመሆኑ ለሀገራት የጋራ ልማት ላይ የሰላም ድልድይ ለመገንባት ያለንን ራዕይ እና ውጥን ለአለም የሚገልጥ ነው ።

የአረንጓዴ ዐሻራ ንቅናቄ ለኢትዮጵያ የካርቦን ልቀትን በመቀነስ የሚከናወን ስነ-ምህዳራዊ ግዴታ ብቻ ሳይሆን፣ የምግብ ዋስትናን የሚያረጋግጥ፣ አረንጓዴ ኢኮኖሚን የሚፈጥር እና ለነገዋ አፍሪካ የስነ-ምህዳር መሪነት መንገድ የሚየጠረግልን የትውልድ ዐሻራ ሆኖ የሚዘልቅ ወሳኝ ሥራችን ነው።- የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review