በመዲናዋ የተከፈቱ ባዛሮች የሸማቾችን የገበያ አማራጭ አስፍተዋል

You are currently viewing በመዲናዋ የተከፈቱ ባዛሮች የሸማቾችን የገበያ አማራጭ አስፍተዋል

AMN- ሚያዚያ 1/2018 ዓ.ም

የትንሳኤ በዓል የፍጆታ ምርቶች ፍላጎት ተደራሽ ለማድረግ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በሁሉም ክፍለ ከተሞች የተከፈቱ የገበያ ባዛሮች የምርት አቅርቦትን ከማሳለጥ ባለፈ የገበያ አማራጭ እያሰፉ መሆናቸውን ነዋሪዎችና አምራቾች ገልጸዋል፡፡

በከተማዋ በሚገኙ 11ቱም ክፍለ ከተሞች ከቀናት በፊት የተከፈቱት ባዛሮች፣ ምርትን በተመጣጣኝ ዋጋ ለህብረተሰቡ በማቅረብ ረገድ ከፍተኛ ድርሻ እያበረከቱ ይገኛሉ።

ኤ ኤም ኤን ቅኝት ባደረገበት በቂርቆስ ክፍለ ከተማ ሜክሲኮ አደባባይ አካባቢ በተከፈተው ባዛር ያነጋገራቸው ሸማቾች እንደገለጹት ፣ በባዛሩ የቀረቡ ምርቶች ከሌሎች መደበኛ የግብይት ስፍራዎች ጋር ሲነፃፀሩ የዋጋ ልዩነት ያላቸውና ለኑሮ ውድነቱ እፎይታ የሚሰጡ ናቸው።

ወይዘሮ መሰረት ስንታየሁ በሰጡት አስተያየት ከነጋዴ ስንገዛ ዋጋው እጥፍ ነው የሚሆነው፤ አሁን ግን እንደ ቲማቲም እና ሽንኩርት ያሉ ምርቶችን በጥሩ ዋጋ እያገኘን ነው ብለዋል። ወይዘሮ አስቴር ሽብሩ በቂ አቅርቦት መኖሩን እና ዋጋዉም ተመጣጣኝ መሆኑን ገልጸዋል።

ምርታቸውን በቀጥታ ለሸማቹ እያቀረቡ ያሉ አምራቾች በበኩላቸው፣ ባዛሮቹ ደላላ የሌለበት የገበያ ትስስር በመፍጠር የተሻለ ገቢ እንዲያገኙ እንደረዷቸው ገልጸዋል።

በስፍራው ምርታቸውን ያቀረቡት አቶ ብስራት አዲስ በመካከላችን ደላላ ስለሌለ እኛም ተጠቃሚ ነን፤ ህብረተሰቡም ምርቱን ያገኛል ሲሉ የገበያ ትስስሩን ፋይዳ አስረድተዋል።

ሌላኛው ምርት አቅራቢ ካሳሁን ፋንታሁን ደግሞ ምርታቸው ሳይበላሽ ለተጠቃሚው መድረሱ ትልቅ ስኬት መሆኑን ጠቁመዋል።

የቂርቆስ ክፍለ ከተማ ዋና ስራ አስፈጻሚ ምስክር ነጋሽ (ዶ/ር) ፣ በክፍለ ከተማው በአሁኑ ወቅት 24 የቅዳሜና እሁድ እንዲሁም የበዓል ባዛሮች አገልግሎት እየሰጡ መሆናቸውንና በስፍራዎቹ ከ176 በላይ ነጋዴዎችና አምራቾች እየተሳተፉ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡

ዋና ስራ አስፈጻሚው እንደ ሽንኩርት እና እንቁላል ያሉ መሰረታዊ የበዓል ግብዓቶች ከከተማ ግብርና እና ከክልል አቅራቢዎች ጋር በተደረገ ትስስር በስፋት እየቀረቡ መሆኑንና ይህም የገበያ ዋጋውን ለመቆጣጠር ከፍተኛ እገዛ ማድረጉን ተናግረዋል፡፡

ባዛሮቹ እስከ በዓሉ ዋዜማ ድረስ ክፍት ሆነው እንደሚቆዩና ህብረተሰቡ የሚፈልጋቸውን ምርቶች በተመጣጣኝ ዋጋ መሸመት እንደሚችል ተመላክቷል።

በታደሠ ሽፈራው

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review