የስቅለት እና የትንሳኤ በዓላት በድምቀትና በስኬት እንዲከበሩ አስፈላጊዉ ቅድመ ዝግጅቶች ተደረገዋል

You are currently viewing የስቅለት እና የትንሳኤ በዓላት በድምቀትና በስኬት እንዲከበሩ አስፈላጊዉ ቅድመ ዝግጅቶች ተደረገዋል

AMN ሚያዝያ 02 ቀን 2018 ዓ/ም

የስቅለት እና የትንሳኤ በዓላት በድምቀትና በስኬት እንዲከበሩ አስፈላጊዉ ቅድመ ዝግጅቶች መደረጋቸዉን ጥምር የፀጥታና ደህንነት የጋራ ግብረ ኃይል አስታዉቋል፡፡

በአዲስ አበባ ፖሊስ ጠቅላይ መምሪያ ልዩ ልዩ የፀጥታ አካላት በተገኙበት የስቅለት እና የፋሲካ በዓላትን አስመልክቶ በተዘጋጀ የፀጥታ እቅድ ላይ ውይይት ተደርጓል።

የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ወንጀል መከላከል ጠቅላይ መምሪያ አዛዥ ምክትል ኮሚሽነር ጀነራል መላኩ ፋንታ የፀጥታና ደህንነት ተቋማት በየጊዜው በሀገራችንም ሆነ በአዲስ አበበባ የተዘጋጁ ታላላቅ ኩነቶች ደህንነታቸው እንዲረጋገጥ ከማድረግ አኳያ ግንባር ቀደም ሚና ወስደው ሲሰሩ እንደነበረ አስታውሰዋል፡፡

የዘንድሮው የስቅለት እና የፋሲካ በድምቀት እንዲከበሩ ዓለም አቀፋዊና ሀገራዊ የፀጥታ ሁኔታን ግምት ውስጥ በማስገባት ማንኛውንም የህግ ጥሰት ለመቆጣጠር በቁርጠኝነት መስራት ከሁሉም የፀጥታ አካላት የሚጠበቅ እንደሆነ የስራ መመሪያ ሰጥተዋል።

የአዲስ አበባ ፖሊስ ጠቅላይ መምሪያ አዛዥ ሌ/ ጀነራል አስራት ደኔሮ በዓላቱ በስኬትና በድምቅት እንዲከበሩ ህዝብ በስፋት በሚንቀሳቀስበት የገበያ ስፍራዎች እና ቤተ-እምነቶች ላይ ልዩ ትኩረት በመስጠት ለህዝብ የፀጥታ ስጋት የሚሆኑ ቦታዎችን በመለየት በቂ ኃይል በመመደብ በየደረጃው ከሚገኙ የፀጥታ አካላት ጋር በመቀናጀት እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

በበዓል ሰሞን ሊከሰቱ የሚችሉ ሀሰተኛ የገንዘብ ዝውውር፣ ማጭበርበሮች፣ ከኪስ ውስጥ ስርቆት እንዲሁም ልዩ ልዩ የምግብ ተዋፅኦዎች ላይ ባዕድ ነገሮችን ቀላቅለው ወደ ገበያ ይዘው የሚወጡ ግለሰቦች ሊኖሩ ስለሚችሉ በግብይት ወቅት ህብረተሰቡ ተገቢውን ጥንቃቄ እንዲያደርግ ጀነራሉ መልዕክት አስተላልፈዋል።

በከተማችን አዲስ አበባ በዓላትን ጠብቀው በተለያየ መልኩ ጫና ለመፍጠር የሚፈልጉ አካላት ያሉ በመሆናቸው ይህን ተረድተን ተገቢ ስምሪት መስጠት ያስፈልጋል ሲሉ የአዲስ አበባ ከተማ ሠላምና ፀጥታ አስተዳደር ቢሮ ኃላፊዋ ወ/ሮ ሊዲያ ግርማ ተናግረዋል።

የስቅለትና የትንሳኤ በዓላት በድምቀት እንዲከበሩ ህብረተሰቡም ከፀጥታ አካላት ጋር በጋራ የመስራት መንፈሱን አጠናክሮ እንዲቀጥልና ህገ-ወጥ የንግድ እንቅስቃሴዎችን ሲመለከት ለሚመለከተው አካል አሳልፎ በመስጠት ኃላፊነቱን ሊወጣ እንደሚገባ የቢሮ ኃላፊዋ አሳሰበዋል።

በበዓል ሰሞን ሊከሰቱ የሚችሉ የወንጀልና ትራፊክ አደጋዎችን አስቀድሞ ለመከላከል የፀጥታ ኃይል በማሰማራት ቴክሎጂን በመጠቀም በተለይም አልኮል ጠጥተው የሚያሽከረክሩና የተለያዩ የደንብ መተላለፍ ጥፋቶችን ለመከላከል በተጠኑ የከተማዋ አካባቢዎች የቁጥጥርና የፍተሻ ስራ ስለሚከናወን ህብረተሰቡ ለጋራ ደህንነት መሆኑን ተገንዝቦ አስፈላጊውን ትብብር ሊያደርግ እንደሚገባ በመድረኩ መገለጹን የአዲስ አበባ ፖሊስ መምሪያ ለኤኤምኤን የላከዉ መረጃ ያመላክታል፡፡

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review