በዘመናዊ የከተማ ልማት እቅድ ውስጥ፣ ስፖርት ከመዝናኛነት አልፎ የከተማዋን የልብ ትርታ የሚቆጣጠር መሰረታዊ የኢኮኖሚና ማህበራዊ አንቀሳቃሽ ኃይል ሆኗል። የዛሬዎቹ ከተሞች የሰውን ልጅ እንቅስቃሴ፣ ማህበራዊ ትስስር እና የጤና ሁኔታ ለማሻሻል የሚያስችላቸውን አቅም የሚገነቡት፣ ስፖርትን ከከተማ መዋቅር ጋር በማዋሃድ ነው። ከተሞች የተጨናነቀ የህይወት ዘይቤ ለማቃለልና የዜጎችን ስነ-ልቦናዊ ደህንነት ለመገንባት ቁልፍ መሳሪያዎች ናቸው።
እንደ ለንደን፣ ኒው ዮርክ እና ሲንጋፖር ያሉ የዓለም ታዋቂ ከተሞች የስፖርት መሰረተ ልማት በማስፋፋትና በከተማ መሃል የሚገኙ ግዙፍ የስፖርት ፓርኮችን በመፍጠር የዜጎችን ጤና ብቻ ሳይሆን የከተማቸውን ውበት እና ኢኮኖሚ ከፍ አድርገዋል። በተለይ በሲንጋፖር ከተማ የሚገኘው ሲንጋፖር ስፖርት ሃብ (Singapore Sports Hub) በዓለም ላይ ካሉ የስፖርት መሠረተ ልማቶች መካከል በግንባር ቀደምትነት የሚጠቀስ ድንቅ የጥበብ ውጤት ነው።
ሲንጋፖር ስፖርትን ከከተማ ልማት ጋር እንዴት እንዳቀናጀች የሚያወሱት የከተማ ፕላን ጥናታዊ ጽሑፎች እንደሚያሳዩት የከተማዋ ስፖርት ሃብ እንዲሁ ስታዲየም ብቻ ሳይሆን፣ ስፖርትን ከንግድ፣ ከመዝናኛ እና ከማህበራዊ ህይወት ጋር ያቆራኘ ‘የከተማ ውስጥ ከተማ’ ነው። በ35 ሄክታር መሬት ላይ ያረፈው ይህ ማዕከል፣ 55 ሺህ ሰዎችን የመያዝ አቅም ያለውን ብሔራዊ ስታዲየም ጨምሮ፤ የውሃ ዋና ማዕከል፣ የቤት ውስጥ ስታዲየም፣ የገበያ አዳራሾች እና የስፖርት ሙዚየምን በአንድ ላይ አቅፏል። ይህ ውህደት ተመልካቾች ለጨዋታ መጥተው በዚያው ግብይት እንዲያደርጉና እንዲዝናኑ የሚያስችል ምቹ ሁኔታ ፈጥሯል።
የስፖርት ሀብ ዶት ኮም ገፀ ድር መረጃ እንደሚያሳየው ይህ የስፖርት ፓርክ ለሲንጋፖር ትልቅ የገቢ ምንጭ ነው። እንደ ወርልድ አትሌቲክስ ሻምፒዮና፣ የእስያ ጨዋታዎች እና ታዋቂ የሙዚቃ ኮንሰርቶችን በማስተናገድ በሺዎች የሚቆጠሩ ቱሪስቶችን ይስባል። ከስፖርታዊ ኩነቶች ባለፈ የንግድ ማዕከላቱ እና ምግብ ቤቶቹ ዓመቱን ሙሉ ክፍት በመሆናቸው፣ ለከተማዋ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ ከፍተኛ ሞተር ሆኖ ያገለግላል።
የሲንጋፖር ስፖርት ፓርክ ለታዋቂ ስፖርተኞች ብቻ ሳይሆን ለሁሉም ዜጎች ክፍት ነው። በማዕከሉ ዙሪያ የሚገኙት የሩጫ መንገዶች፣ የብስክሌት መስመሮች እና በውሃ ዳርቻ ላይ የሚገኙ የመዝናኛ ስፍራዎች ነዋሪዎች የጤናማ ህይወት ዘይቤን እንዲከተሉ ያበረታታሉ። ቤተሰቦች ቅዳሜና እሁድን የሚያሳልፉበት፣ ወጣቶች የሚለማመዱበት እና አረጋውያን የእግር ጉዞ የሚያደርጉበት የጋራ የመገናኛ ድልድይ ሆኖ ያገለግላል።
ዛሬ ላይ አዲስ አበባም አዲስ የስፖርት ፓርክ በመገንባት ይህንን ጎዳና ተከትላለች። በ5 ነጥብ 7 ሄክታር መሬት ላይ ያረፈውና በኦሎምፒክ መድረክ ለኢትዮጵያ የወርቅ ሜዳሊያ ያስገኙ 15 አትሌቶችን የሚዘክሩ የክብር ሐውልቶች በፓርኩ መሃል ያቆመው ይህ ፓርክ ሰሞኑን ተመርቆ ለአገልግሎት ክፍት ሆኗል፡፡ የኦሎምፒክ ደረጃውን የጠበቀ የመዋኛ ገንዳ፣ ደረጃቸውን የጠበቁ የእግር ኳስ፣ የቅርጫት ኳስ እና የሜዳ ቴኒስ መሰረተ ልማቶች፣ የ800 ሜትር የሩጫ ትራክ ማዕከሉ ዓለም አቀፍ መስፈርቶችን እንዲያሟላ ተደርጎ ተገንብቷል፡፡
ፕሮጀክቱ ከላቀ የስፖርት አገልግሎት ባለፈ፣ በልማቱ ምክንያት ለተነሱ የህብረተሰብ ክፍሎች የኢኮኖሚ አቅም የሚሆኑ 105 አዳዲስ የንግድ ሱቆች እና 3 ሺህ ሰዎችን ማስተናገድ የሚችል ሰፊ ፕላዛ ይዟል። እንደዚሁም በአንድ ጊዜ 300 መኪናዎችን የሚይዝ ባለ ሁለት ወለል የምድር ቤት መኪና ማቆሚያ በውስጡ አካቷል፡፡
በአዲስ አበባ ከተማ ሰሞኑን የተመረቀው ዘመናዊ የስፖርት ፓርክ፣ የከተማዋን ገጽታ ከመቀየር ባለፈ ለነዋሪዎቿ ጤናማና ንቁ የአኗኗር ዘይቤን በማምጣት ረገድ ትልቅ ምዕራፍ ተደርጎ ይወሰዳል። ይህ ፕሮጀክት በከተማ ልማትና በስፖርት መሰረተ ልማት መካከል ያለውን ጥብቅ ቁርኝት በተግባር ያሳየ ሲሆን፣ በተለይም ወጣቶችና የስፖርት አፍቃሪዎች በቅርብ ርቀት ደረጃቸውን የጠበቁ ማዘውተሪያዎችን እንዲያገኙ ያስችላል።
ፓርኩ ዘመናዊ የእግር ኳስ ሜዳዎችን፣ የቅርጫት ኳስና የቮሊቦል መጫወቻዎችን እንዲሁም የሩጫና የብስክሌት መሄጃዎችን በአንድ ላይ አቀናጅቶ የያዘ ነው። ይህ መሰረተ ልማት ነዋሪዎች ከስራ ጫና ወጥተው የሚያርፉበት፣ አካላዊ ብቃታቸውን የሚያሳድጉበትና ማህበራዊ ትስስራቸውን የሚያጠናክሩበት ‘የከተማዋ ሳንባ’ ሆኖ ያገለግላል። ከዚህም ባለፈ፣ ፕሮጀክቱ የአካባቢውን ውበት ከመጠበቅና አረንጓዴ ልማትን ከማስፋፋት አኳያ ለከተማዋ የረጅም ጊዜ እድገት የላቀ ፋይዳ አለው።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ፓርኩን መርቀው በከፈቱበት ወቅት እንደገለፁት “የከተማችንን እድሳት ለማፋጠን እና የዜጎቻችንን ክብር ለመመለስ የገባነውን ቃል አንዱ ማረጋገጫ የሆነውን የአዲስ ስፖርት ፓርክን በይፋ መርቀን ከፍተናል” ብለዋል፡፡
በ5 ነጥብ 7 ሄክታር መሬት ላይ ያረፈው ይህ ፕሮጀክት፤ በኦሎምፒክ መድረክ ለሀገራችን የወርቅ ሜዳሊያ ያስገኙ 15 አትሌቶችን የሚዘክሩ የክብር ሐውልቶችን በፓርኩ መሃል በማቆም፣ የጀግኖቻችን ታሪክ ለተተኪ ትውልድ ስፖርተኞች ተምሳሌት ሆኖ እንዲቀጥል ያደርጋልም ብለዋል ጠቅላይ ሚኒስትሩ።
የአዲ አበባ ከተማ ከንቲባ ወይዘሮ አዳነች አቤቤ በምረቃው ወቅት እንደገለጹት፣ እንዲህ ያሉ ፕሮጀክቶች የከተማዋን ነዋሪዎች የኑሮ ጥራት ለማሻሻል ካላቸው ቁርጠኝነት የሚመነጩ ናቸው።
ከንቲባዋ ባስተላለፉት መልዕክት፣ “ይህ የስፖርት ፓርክ ለወጣቶቻችን የስፖርት መክሊታቸውን የሚያሳድጉበት ብቻ ሳይሆን፣ ጤናማና አምራች ትውልድ የምንገነባበት ማዕከል ነው” ብለዋል።
ትውልዱን ለመገንባት የያዝነውም ራዕይ የምንተገብርበት ስፍራ ጭምር ነው ያሉት ከንቲባ አዳነች፣ ኢትዮጵያን በዓለም ደረጃ ስሟን የሚያስጠሩ ወጣቶች የሚፈጠሩበትና የሚሰለጥኑበት ቦታ ስለመሆኑም ገዋፀዋል፡፡ አክለውም፣ ከተማዋን ለነዋሪዎቿ ምቹ ለማድረግ የሚከናወኑ የኮሪደር ልማትና መሰል የልማት ስራዎች ስፖርትንና ጤናማ እንቅስቃሴን ማዕከል ማድረጋቸውን እንደሚቀጥሉ አረጋግጠዋል።
በአዲስ ስፖርት ፓርክ የምረቃ እና ጉብኝት መርሐ ግብር ላይ የተገኘው አትሌት ቀነኒሳ በቀለ በበኩሉ፣ የልማት ስራው ለሀገር ያለውን ዘርፈ ብዙ ፋይዳ አስመልክቶ ምስክርነቱን ሰጥቷል። አትሌት ቀነኒሳ በተለያዩ የዓለም ሀገራት ለውድድር በሚጓዝበት ወቅት በከተሞቻቸው ውስጥ ትላልቅ ፓርኮችና ማህበረሰቡ ስፖርታዊ እንቅስቃሴዎችን የሚያደርግባቸው ሜዳዎች ከፍተኛ የቅናት ስሜት ያሳድሩበት እንደነበር ገልጿል። እንደ አትሌቱ ገለጻ፣ ስፖርት የአንድ ሀገር የጀርባ አጥንት ሲሆን፣ ይህም ዜጎች እንደ ስኳርና የደም ግፊት ካሉ ስር የሰደዱ በሽታዎች ራሳቸውን እንዲጠብቁ ይረዳቸዋል ይላል።
በተጨማሪም ህዝቡ በጤና እጦት ምክንያት ለመድኃኒት የሚያወጣውን ወጪ የሚቀንስ ሲሆን፣ ሀገርም ለህክምና ግብዓቶች የምታወጣውን የውጭ ምንዛሬ እንድታድን በማድረግ ጤናማና አምራች ዜጋ ለመፍጠር ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያበረክታል ብሏል።
የስፖርት ጋዜጠኛ ኤፍሬም የማነህ በማህበራዊ ትስስር ገፁ ባሰፈረው ጽሑፍ እንዳለው በየሰፈሩ በብዛት እየተሰሩ ካሉ ምቹ ሜዳዎች ባሻገር እንደ ካዛንቺሱ የስፖርት ፓርክ ዐይነቶቹ የነገ የትውልድ አሻራ ህያው ቀለሞች ሆነው ይጠቀሳሉ ይላል። በዓለም መድረክ የኩራታችን ሚስጥር የሆኑ ጀግኖች አትሌቶቻችንን በአግባቡ የሚዘክር እና ለትውልድ መነቃቃት በሚሆን መልኩ ያውም መሬት ወርዶ መታየቱ ኮኮቦችን ለመፈጠር ታላቅ ሚና አለው ይላል፡፡
ይህ የስፖርት ፓርክ ከስፖርታዊ እንቅስቃሴ ባለፈ ሰፊ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ፋይዳዎችን ይዟል። በተለይም በከተማዋ የሚስተዋለውን የማዘውተሪያ ስፍራዎች እጥረት በመቅረፍ፣ ወጣቶች ጊዜያቸውን በአግባቡና ውጤታማ በሆነ መንገድ እንዲያሳልፉ ምቹ ሁኔታ ይፈጥራል። ፓርኩ ለተለያዩ ስፖርታዊ ውድድሮችና ማህበራዊ ኩነቶች መድረክ በመሆን የከተማዋን የ24 ሰዓት እንቅስቃሴ (24-hour cycle) የሚያነቃቃ ሲሆን፣ ይህም ለአካባቢው አነስተኛ ንግዶች መነቃቃትና ለአዳዲስ የስራ እድሎች ፈጠራ የራሱን አዎንታዊ አሻራ ያሳርፋል።
በሳህሉ ብርሃኑ