AMN-ሚያዝያ 6/2018 ዓ.ም
የአውሮፓ ቻምፒየንስ ሊግ የሩብ ፍፃሜ የመልስ ጨዋታዎች ዛሬ ይጀምራሉ። ሊቨርፑል እና ባርሰሎና የመጀመሪያ ሽንፈታቸውን ለመቀልበስ የሚያደርጉት ትንቅንቅ ይጠበቃል።
ሊቨርፑል በሜዳው አንፊልድ ፓሪሰን ዠርማ ሲያስተናግድ በመጀመሪያው ጨዋታ የደረሰበትን የ2ለ0 ሽንፈት ለመቀልበስ ይፋለማል።
ቀዮቹ በፓርክ ደ ፕራንስ 2ለ0 ሲሸነፉ ያሳዩት ብቃት ደካማ ነበር ፤ አሰልጣኙ አርነ ስሎት እንዳሉትም ፒ ኤስ ጂ ከነበረው ብልጫ መነሻ ጨዋታው 2ለ0 ብቻ መጠናቀቁ ዕድለኛ ያደርጋቸዋል። የመርሲሳይዱ ክለብ በፓሪስ ባደረገው በዚህ ጨዋታ አንድም ኢላማውን የጠበቀ ሙከራ እንኳን ማድረግ አልቻለም ነበር።
ሊቨርፑል ውጤቱን ለመቀልበስ ከመጀመሪያው ጨዋታ በእጅጉ የተሻለ ብቃት ማሳየት ይጠበቅበታል።
የሊውስ ኤነሪኬው ፓሪሰን ዠርማ አሁንም በምርጥ ብቃቱ ላይ ይገኛል። በሳምንቱ መጨረሻ ከሎንስ ጋር ሊያደርገው የነበረው የፍሬንች ሊግ ኧ ተጠባቂ ጨዋታ ለሌላ ጊዜ በመሸጋገሩ አንፊልድ የደረሰው በቂ እረፍት አግኝቶ ኘው። ሊቨርፑል በአንፃሩ በእንግሊዝ ፕሪምየር ሊግ ከፉልሃም ጋር ተጫውቶ 2ለ0 ማሸነፉ ይታወሳል።

ሁለቱ ክለቦች በአጠቃላይ ሰባት ጊዜ ተገናኝተው ፓሪሰን ዠርማ በአራቱ የበላይ ሆኖ ሲያጠናቅቅ ፣ ሊቨርፑል በሦስቱ ድል አስመዝግቧል። ለመጨረሻ ጊዜ ባለፈው ዓመት በጥሎ ማለፍ ዙር ሲገናኙ ሊቨርፑል በፓርደ ፕራንስ ፣ ፒ ኤስ ጂ ደግሞ በአንፊልድ በተመሳሳይ የ1ለ0 ድል ማስመዝገባቸው ይታወሳል። የፈረንሳዩ ክለብ በመለያ ምት አሸንፎ በማለፍ የውድድር ዓመቱን ዋንጫውን በማንሳት አጠናቋል።
የዛሬ ስምንተኛ ጨዋታቸው ምሽት 4 ሰዓት ሲጀምር ጣልያናዊው ዋና ዳኛ ማውሪዚዮ ማሪአኒ ይመሩታል።
በሌላ ጨዋታ አትሌቲኮ ማድሪድ በዋንዳ ሜትሮፖሊታኖ ባርሰሎናን ያስተናግዳል። ሁለቱ የስፔን ሃያላን ክለቦች በካምፕ ኑ ያደረጉት የመጀመሪያ ጨዋታ በአትሌቲኮ 2ለ0 አሸናፊነት ተጠናቆ ነበር። ባርሰሎና በጨዋታው ተከላካዩ ፓኡ ኩፓርሲን 44ኛው ደቂቃ ላይ በቀይ ካርድ ማጣቱ ዋጋ አስከፍሎታል።
ባርሰሎና ውጤቱን የመቀልበስ አቅም እንዳለው አሰልጣኙ ሀንሲ ፍሊክ ከጨዋታው በፊት በነበራቸው መግለጫ ተናግረዋል።

ለካታሎኑ ክለብ ፈታኙ ነገር በቻምፒየንስ ሊግ ታሪክ አንድ ቡድን በሜዳው ሁለት እና ከዚያ በላይ ተቆጥሮባቸው ሽንፈት ከተመዘገበባቸው 194 አጋጣሚዎች ውጤቱ የተቀለበሰው ሁለት ጊዜ ብቻ ነው። ይህም በ1968/69 አያክስ ቤኔፊካን ፤ 2018/19 ማንችስተር ዩናይትድ ፓሪሰን ዠርማ አሸንፈው ያለፉበት ብቻ ነው የሚጠቀሰው።
ባርሰሎና ይህን ታሪክ የሚጋራ ሦስተኛው ክለብ ይሆናል? ምሽት 4 ሰዓት በፈረንሳዊው ዋና ዳኛ ክሌሞን ተርፓን ፊሽካ የሚጀምረው ጨዋታ ምላሽ ይሰጠናል።
በሸዋንግዛው ግርማ