በኢትዮጵያ የሚከናወኑ የልማት ስራዎች የግል ዘርፉን ተሳትፎ በማሳደግ ረገድ ውጤት እያስገኙ ነው – ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)

You are currently viewing በኢትዮጵያ የሚከናወኑ የልማት ስራዎች የግል ዘርፉን ተሳትፎ በማሳደግ ረገድ ውጤት እያስገኙ ነው – ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)

AMN – ሚያዝያ 11/2018 ዓ.ም

በኢትዮጵያ የጠራ ፖሊሲ መኖርና በየተቋማቱ የማስፈጸም አቅም እየተገነባ በመምጣቱ በተለያዩ የኢኮኖሚ ዘርፎች ላይ ተጨባጭ ውጤቶች እየተመዘገቡ መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገለጹ።

በተለይም አምስቱ ዋና ዋና የኢኮኖሚ ምሰሶዎች ተብለው በተለዩት የኢንዱስትሪ፣ የግብርና፣ የማዕድን፣ የቴክኖሎጂ እና የቱሪዝም ዘርፎች ላይ የግል ባለሀብቶች በስፋት እንዲሳተፉ በተደረገው ጥረት በሀገር ውስጥ ምርት እድገትና ለውጭ ምንዛሬ ግኝት ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያበረከተ መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትሩ አብራርተዋል።

በሐሮ ደንዲ ሎጅ ተገኝተው ባደረጉት ንግግር ፣ ቀደም ሲል በመንግስት ብቻ ተይዘው የነበሩ እንደ ኢንዱስትሪ ፓርክ ግንባታ ያሉ ስራዎች አሁን ላይ በግል ባለሀብቶች ጭምር እየተከናወኑ መሆናቸውንም ጠቅሰዋል።

በግብርናው ዘርፍም በሚሊዮን የሚቆጠሩ አርሶ አደሮችን በክላስተር በማደራጀትና ዘመናዊ ማሽነሪዎችን በማቅረብ ምርታማነት እንዲጨምር መደረጉን ያነሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ይህም የግል ዘርፉ በዘመናዊ ግብርናና በመስኖ ልማት ላይ በስፋት እንዲሰማራ መንገድ መክፈቱን አስረድተዋል።

በማዕድን ዘርፍም በወርቅ፣ በማዳበሪያ፣ በጋዝ እና በሲሚንቶ ምርት ላይ የግል ዘርፉ ተሳትፎ እያደረገ ያለው ተሳትፎ የሚበረታታ መሆኑን የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ፣ በቴክኖሎጂው ዘርፍም በቴሌኮም ገበያ ውስጥ ውድድር እንዲፈጠር መደረጉና የዳታ ተደራሽነት ማደጉ ኢኮኖሚውን እያነቃቃው መሆኑን ገልጸዋል።

በቱሪዝም ዘርፍም ሀገራችን በርካታ የቱሪስት መስህቦች እንዳሏት ያነሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ባለሀብቱን በማስተባበር የተገነቡት እንደ ገበታ ለሀገር እና ገበታ ለሸገር በመሳሰሉ ፕሮጀክቶች አማካኝነት ከዚህ በፊት የነበሩ የመሠረተ ልማት ችግሮች እየተቀረፉ መሆናቸውንም ተናግረዋል፡፡

በቀጣይ የሚካሄደውን የኮፕ 32 ጉባኤን ለመታደም ወደ ኢትዮጵያ የሚመጡትን እንግዶች በተሟላ ሁኔታ ለማስተናገድ የሀገሪቱን የሆቴል አልጋዎች አቅም ከ20 ሺህ ወደ 80 ሺህ ከፍ ለማድረግ የሚስተዋለው የባለሀብቶች ተሳትፎ የተቀመጠው ፖሊሲ ፍሬ እያፈራ መሆኑን የሚያሳይ እንደሆነ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) አስገንዝበዋል።

በወርቅነህ አቢዮ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review