AMN- ሚያዝያ 14/2018 ዓ.ም
የአገልግሎት አሰጣጥ ሥርዓቱ በቴክኖሎጂ እንዲታገዝ በማድረግና የመሶብ አገልግሎት በመጠቀም ስር ነቀል ለውጥ እየመጣ መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገለጹ።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ተንቀሳቃሽ የመሶብ አገልግሎት መጀመሩን አስመልክቶ በሰጡት ማብራሪያ፣ ኢትዮጵያ ውስጥ ከቆዩት ዋና ዋና ማነቆዎች አንዱ የተገልጋዮችን እርካታ ማረጋገጥ አለመቻል ሲሆን፣ ይህንን ችግር ለመፍታት ቴክኖሎጂን እንደ አምስተኛ የልማት ምሰሶ በመጠቀም ውጤታማ ሥራዎች እየተከናወኑ ይገኛሉ ብለዋል።
ቀደም ሲል በአንድ ማዕከል የተጀመረው አገልግሎት በአሁኑ ወቅት ወደ 45 ማዕከላት ያደገ ሲሆን፣ እስከ መስከረም ወር ድረስ ከመቶ በላይ ማዕከላት አገልግሎት መስጠት እንደሚጀምሩ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ገልጸዋል።
በተለይም በአሁኑ ወቅት የተጀመረው በኤሌክትሪክ የሚሰሩ ተንቀሳቃሽ መኪናዎች አገልግሎት ዜጎች ባሉበት አካባቢ ሆነው ፓስፖርት፣ የንግድ ፈቃድ እና የልደት ምስክር ወረቀቶችን ጨምሮ በርካታ አገልግሎቶችን በቀላሉ እንዲያገኙ እንደሚያስችላቸው ተናግረዋል።

አገልግሎት ከታነቀ ብልጽግና ማረጋገጥ አይቻልም ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ በትራፊክ ማኔጅመንት እና በዲጂታል አገልግሎት ከእያንዳንዱ ዜጋ በቀን 10 ደቂቃ ማትረፍ ቢቻል፣ ያ የተረፈ ጊዜ ለሀገር ምርታማነት ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው አስረድተዋል።
ይህ የሪፎርም ጉዞ ቀላል እንዳልነበረና የቆየውን አሰልቺ ተቋማዊ ባህል የመቀየር ትልቅ ፈተና እንደነበረ ጠቅሰው፣ በአሁኑ ወቅት የመጣው ለውጥ ተስፋ ሰጪ መሆኑንና በቀጣይ ሁለት እና ሶስት ዓመታት ውስጥ ዜጎች ካሉበት ስፍራ ሆነው ሁሉንም አገልግሎቶች እንዲያገኙ በትኩረት እንደሚሰራ አረጋግጠዋል።
በታደሠ ሽፈራው