AMN – ግንቦት 12/2018 ዓ.ም
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ማኅበራዊ ፍትሕን ለማረጋገጥና አቅመ-ደካማ ዜጎችን ለመደገፍ ካከናወናቸው ዘላቂና ስኬታማ ሥራዎች መካከል ከ2012 ዓ.ም. ጀምሮ በይፋ የተጀመረው የተቀናጀ የምገባ መርሃ-ግብር በግንባር ቀደምትነት ይጠቀሳል።
ይህ መርሃ-ግብር ቀደም ሲል በተበታተነ መልኩ ይካሄድ የነበረውን የበጎ አድራጎት ሥራ ወደ ተቋማዊ አሠራር በመቀየር ረገድ አዲስ የታሪክ ምዕራፍ ከፍቷል።
የመርኃ-ግብሩ የመጀመሪያ ምዕራፍ የተጀመረው በመንግሥት ትምህርት ቤቶች የሚማሩ ተማሪዎችን ተጠቃሚ በማድረግ ነበር።
በመንግሥት በጀት የሚደገፈው ይህ ታሪካዊ እርምጃ፤ ተማሪዎች በባዶ ሆዳቸው ወደ ትምህርት ቤት ከመምጣታቸው ጋር ተያይዞ ይከሰት የነበረውን የትምህርት ማቋረጥና ከክፍል መቅረት ችግር በዘላቂነት መፍታት ችሏል።
በሂደትም ፕሮግራሙ እያደገ በመምጣቱ ተማሪዎች ከተማ አስተዳደሩ ከሚያቀርብላቸው የመማሪያ ቁሳቁስና ጫማ በተጨማሪ በየዕለቱ የተመጣጠነ ቁርስና ምሳ እንዲያገኙ እየተደረገ ይገኛል።

ይህ ጅምር ባለፉት ዓመታት በከተማችን የነበረውን አሳዛኝ የባዶ ምሳ ዕቃ ታሪክ የቀየረ፣ የወላጆችን ሸክም ያቀለለ እና የተማሪዎችን ውጤት በከፍተኛ ሁኔታ ያሻሻለ አኩሪ ተግባር ሆኗል።
የተማሪዎችን ምገባ ስኬት ተከትሎ አስተዳደሩ ድጋፉን ይበልጥ በማስፋት አቅመ-ደካማ፣ አዛውንቶችና ዝቅተኛ ገቢ ያላቸውን ነዋሪዎች ያካተተ የማኅበረሰብ ምገባ መርሃ-ግብር በይፋ ጀምሯል።
በተለይም በከንቲባ አዳነች አቤቤ ከፍተኛ ትኩረት ተሰጥቶት በሜጋ ፕሮጀክት ደረጃ መካሄድ የጀመረው ይህ መርሃ-ግብር “ተስፋ ብርሃን” በሚል ስያሜ ሥራውን አጠናክሮ ቀጥሏል።

በየክፍለ ከተማው በተገነቡ 29 ዘመናዊ የምገባ ማዕከላት አማካኝነት በአሥር ሺዎች የሚቆጠሩ አቀመ ደካማና ድጋፍ የሚፈልጉ ዜጎች በየቀኑ የተመጣጠነ ምግብ እንዲያገኙ ተደርጓል።
በማዕከላቱ በሺዎች የሚቆጠሩ ዝቅተኛ ገቢ ያላቸው የአካባቢው እናቶች በምግብ ዝግጅትና በጽዳት ሥራዎች ላይ ተሰማርተው ራሳቸውንና ቤተሰባቸውን በቋሚነት እንዲደግፉም የሥራ ዕድልን ፈጥሯል።
የመንግሥትን፣ የባለሀብቶችንና የሕብረተሰቡን አቅም ባስተባበረ መልኩ የሚመራው ይህ የተቀናጀ የምገባ መርሃ-ግብር ፣ አዲስ አበባን ለነዋሪዎቿ ምቹ፣ ዘመናዊና አረንጓዴ ከማድረግ ጎን ለጎን ሰብአዊነትና ማኅበራዊ ፍትሕን ያስቀደመ የልማት ጉዞ እየተከተለች መሆኗን ማሳያ ነው።
በበረከት ጌታቸው