ኢትዮጵያ በአህጉሩ የሰው ሰራሽ አስተውሎትንና የፈጠራ ሥራዎችን ለማስፋፋት እየተገበረች ለምትገኘው የላቀ ሚና የተሰጠ እዉቅና

You are currently viewing ኢትዮጵያ በአህጉሩ የሰው ሰራሽ አስተውሎትንና የፈጠራ ሥራዎችን ለማስፋፋት እየተገበረች ለምትገኘው የላቀ ሚና የተሰጠ እዉቅና

AMN ሚያዝያ 15/2018 ዓ.ም

መንግስት ከፍተኛና ልዩ ትኩረት ከሰጣቸዉ ዘርፎች አንዱ የሰው ሰራሽ አስተውሎት (AI) ዘርፍ ሲሆን ቴክኖሎጂዉ ፈጣን ለውጥ እያሳየ ይገኛል፡፡

ቴክኖሎጂው ተግባራዊ ከተደረገባዉቸዉ ዘርፎች መካከል የትምህርትና ምርምር ተቋማት የመጀመሪያዎቹ ሲሆኑ የሚኒስትሮች ምክር ቤት የሰው ሰራሽ አስተውሎት ዩኒቨርሲቲ እንዲቋቋም ረቂቅ አዋጅ አጽድቋል።

ይህ ዩኒቨርሲቲ በሮቦቲክስ፣ በማሽን ለርኒንግ እና በዳታ ሳይንስ ዘርፎች ተማሪዎችን ለማሰልጠን የታለመ ነዉ፡፡

የ5 ሚሊዮን ኮደርስ ወጣቶችን በዲጂታል ክህሎትና በኮዲንግ በማሰልጠን ለታቀደው ለAI ዘርፍ መሰረት እየጣለ ይገኛል።

የኢትዮጵያ አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩትም ቴክኖሎጂዉን በጤና፤ በግብርና፤ በቋንቋ፤ በስማርት አገልግሎትና መሰል ዘርፎች ላይ ተግባራዊ በማድረግ ቴክኖሎጂዉን በማላቅ ላይ ይገኛል፡፡

የAI ቴክኖሎጂዎች በጤናዉ ዘርፍ የጡት ካንሰርን፣ የስኳር በሽታንና የቆዳ በሽታዎችን ቀድሞ ለመለየት የሚያስችሉ ሲሆኑ በግብርናዉ ዘርፍ የቡና ተክል በሽታዎችን በምስል በመለየት በመተግበሪያ ለአርሶ አደሮች መረጃ የሚሰጡ ናቸዉ፡፡

የአማርኛና ሌሎች የሀገር ውስጥ ቋንቋዎችን በንግግር እና በትርጉም ዘርፍ ወደ ዲጂታል ለማስገባት በርካታ ተግባራት በመከናወን ላይ እንደሚገኙ መረጃዎች ያመላክታሉ፡፡

መንግስት የአገልግሎት አሰጣጡን ቀልጣፋ፤ ከሙስናና ከአድልዎ ነጻ ለማድረግ እንደ “መሶብ” ያሉ የአንድ ማዕከል አገልግሎቶች AIን በመጠቀም አዲስ አበበን ጨምሮ በተቀሩት ክልሎች ተግባራዊ ለማድረግ እየሠራ ይገኛል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) እና ከንቲባ አዳነች አቤቤ በቅርቡ አገልግሎት ያስጀመሩት የአዲስ አበባ “በአዲስ መሶብ ዲጅታል የአንድ ማዕከል ተንቀሳቃሽ አውቶቡስም የዚሁ ቴክኖሎጂ አንዱ ገጸ በረከት ነዉ፡፡

ሃገሪቱ የሰው ሰራሽ አስተውሎትን ለኢኮኖሚ እድገትና ለህዝብ አገልግሎት ማሳለጫነት ለመጠቀም ከፍተኛ ጥረት እያደረገችም ትገኛለች፡፡

ኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት የአፍሪካ ህብረት የሰው ሰራሽ አስተውሎትና የዲጂታል ጤና “ቻምፒዮን” በመሆን አህጉራዊ የፖሊሲ ቀረጻዎችን እየመራች የምትገኝ ሲሆን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በአፍሪካ ሕብረት የሰው ሰራሽ አስተውሎት እና የዲጂታል ጤና ዘርፍ መሪ (Champion) ሆነው ተሹመዋል፡፡

ሹመቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በዘርፉ ላሳዩት አመራር እና ኢትዮጵያ በአህጉሩ የሰው ሰራሽ አስተውሎትንና የፈጠራ ሥራዎችን ለማስፋፋት እየተገበረች ለምትገኘው የላቀ ሚና እውቅና የሚሰጥ ነዉ፡፡

የሰው ሰራሽ አስተውሎት (AI) በኢትዮጵያ ተስፋ ሰጪ ዉጤቶችን እያስመዘገበ የሚገኝ ዘርፍ ሲሆን፣ ዘርፉ የሚፈልገዉን በቂ የሰዉ ሃይል ለማፍራት፤ ከፍተኛ ኮምፒውቲንግ መሰረተ ልማት ለመዘርጋት፤ የዳታ ጥራትና የሳይበር ደህንነት ስጋቶችን ለመቅረፍም በትኩረት እየተሰራ ይገኛል፡፡

በወንድማገኝ አሰፋ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review